በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሴኔጋል ምርጫ የገዢው ፓርቲ ወኪል ለተቃዋሚው እጩ ድል እውቅና ሰጡ


የሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊ እጩ ባሲሩ ፋዬን ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለፁ በዳካር፣ ሴኔጋል፣ እአአ መጋቢት 24/2024
የሴኔጋል ፕሬዚዳንታዊ እጩ ባሲሩ ፋዬን ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለፁ በዳካር፣ ሴኔጋል፣ እአአ መጋቢት 24/2024

ሴኔጋላውያን አጠቃላዩን የምርጫ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ባሉበት በዚህ ወቅት፡ የገዢው ፓርቲ እጩ የሆኑት አማዱ ባ፣ ለተቃዋሚው እጩ ባሲሩ ፋዬ ድል እውቅና በመስጠት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ኦፊሴላዊ የምርጫውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ ብንሆንም፣ እስከ አሁን የታዩትን ውጤቶች በመመልከት፣ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በማሸነፋቸው ፕሬዝደንት ባሲሩ ፋዬን እንኳን ደስ አለዎት ማለት እሻለሁ” ሲሉ አማዱ ባ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሴኔጋላውያን ከወራት ሁከት በኋላ በሰላማዊ መንገድ የተጠናቀቀውን የትናንት እሁድ ምርጫ አጠቃላይ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

በመፈንቅለ መንግስት በተናጠው የምዕራብ አፍሪካ ቀጠና የመረጋጋት ምሳሌ የነበረችው ሴኔጋል፣ የፕሬዝደንት ማኪ ሳል መንግሥት ምርጫውን ለማራዘም መወሰኑን ተከትሎ ቀውስ ውስጥ ገብታ ነበር።

የአገሪቱ የሕገ መንግሥት ም/ቤት የመንግሥትን ውሳኔ በመሻር ምርጫው ትናንት እንዲደረግ ወስኗል።

በምርጫው ከፍተኛ የድምጽ ሰጪዎች ቁጥር እንደታየ ታዛቢዎች በመናገር ላይ ናቸው።

ቆጠራው በተጠናቀቀባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውጤቱ ሌሊቱን በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቀ ሲሆን፣ አጠቃላዩ የምርጫ ውጤት ሣምንቱ ከማለቁ በፊት እንደሚታወቅ ይጠበቃል።

በተቃዋሚው እጩ ባሲሩ ፋዬ እና የገዢው ፓርቲ እጩና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑት አማዱ ባ መካከል አሸናፊውን ለመለየት ድጋሚ ምርጫ ሊያስፈልግ ይችላል ሲሉ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።

የተቃዋሚው እጩ ደጋፊዎች አሸናፊነታቸውን በመግለጽ በዳካር አውራ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል ሲል ኤኤፍፒ ከስፍራው ዘግቧል።

ከስድሳ ዓመታት በፊት ከፈረንሣይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣቸው ሴኔጋል፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስታካሂድ ይህ አራተኛ ጊዜዋ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG