በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስለ ዶ/ር መምህርት ማይገነት ሺፈራው


ዶ/ር መምህርት ማይገነት ሺፈራው /
ዶ/ር መምህርት ማይገነት ሺፈራው /

ዶ/ር ማይገነት ሺፈራው በ69 ዓመት ዕድሜአቸው አልፈው አስከሬናቸው ባለፈው ሣምንት ሜሪላንድ ውስጥ አርፏል።

ዶ/ር ማይገነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አርሲ ክፍለሃገር በሚገኘው ደጃች ዳርጌ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አሠላ ካጠናቀቁ በኋላ ሐረር ከሚገኘው የመምህራን ማሠልጠኛ ተመርቀዋል።

የመምህርነት ሙያቸውን አዲስ አበባ ደጃች ዑመር ሰመተር ት/ቤት ጀምረው በልማት ባንክና በአሜሪካው የዓለምአቀፍ ልማት ተቋም - ዩኤስኤአይዲ ውስጥ ሠርተዋል።

ማይገነት በሥርዓተ-ትምህርት የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎቻቸውን ዋይት ዋተር በሚገኘው ዊስካንሰን ዩኒቨርሲቲ ሠርተዋል። ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በትምህርት ሚኒስቴር በጎልማሶች ትምህርት ተቋም ውስጥ ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል።

ወደ አሜሪካ ተመልሰው ሚልዋኪ ከተማ በሚገኘው የዊስካንሰን ዩኒቨርሲቲ ተቋም ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ሠርተዋል። ዶ/ር ማይገነት ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ዝግጅት ከአሜሪካ የዩኒቨርሲቲ ሴቶች ማኅበር ባገኙት ድጋፍ ለጥናታቸው መንደርደሪያ የሚሆን ፅሁፍ ለማዘጋችት ወደ ዋሺንግተን ዲ.ሲ በመጡበት ወቅት በኮንግረሱ ቤተ-መፃሕፍት ለምርምር ሲመላለሱ ከተወዋወቋቸው የወደፊት የትዳር ጓደኛቸው ከዶ/ር ጌታቸው መታፈሪያ ጋር ወደ ዛምቢያ ተጉዘው መንግሥቱ የሴቶችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በሚመለከት የሚያወጣውን ፖሊሲ አጥንተዋል።

ዶ/ር መምህርት ማይገነት ሺፈራው
ዶ/ር መምህርት ማይገነት ሺፈራው

ዶ/ር ማይገነት በዓለም ባንክና በትምህርት ተቋማት ውስጥ የፖሊሲ ሠነዶችን በማዘጋጀት፣ በምርምርና በማስተማር አገልግለዋል። በመጨረሻም በዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በጎልማሶች ትምህርት መስክ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ሲሰጡ ቆይተዋል። ዶ/ር ማይገነትና ባለቤቷ ዶ/ር ጌታቸው “The Ethiopian Revolution of 1974 – The Exodus of Ethiopian Trained Human Resource” የሚል መፅሐፍ በጋራ አዘጋጅተው አሣትመዋል።

በተጨማሪም ዶ/ር ማይገነት “The Struggle from Afar: Our Journey for Peace Movement” በሚል ርዕስ መፅሐፍ አዘጋጅተው ለሕትመት ተሰናድቶ ይገኛል። ከዚህም ሌላ ዶ/ር ማይገነት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ፅሁፎችና መጣጥፎች በኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ነክ ጉዳዮች ላይ ፅፈዋል፤ ለሕትመትና ለንባብ አብቅተዋል። ድኅነትን እንዲጠፋ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ዲሞክራሲ እንዲፀና ትምህርትና ብቃት ያላቸው የሲቪክ መሪዎች መኖራቸው እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ማይገነት አጥብቀው ያምኑ ነበር።

በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያ አሜካዊያንን አቅምና ብቃት በማጎልበትም ሰፊ ተሣትፎ የነበራት ዶ/ር ማይገነት በዋሺንግተን ዲ.ሲ. የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ማዕከል ውስጥ ትምህርትና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

ከሌሎች ኢትዮጵያዊያት ወገኖቻቸው ጋር ሆነው “የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል” እንዲሁም “የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላምና የልማት ድርጅት” የሚባሉ የሴቶች መብቶችና ደኅንነት ተሟጋች ማዕከሎችን መሥርተው ኢትዮጵያ ውስጥና በውጭ ሃገሮች ለሚንገላቱ ድምፅ የለሽ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ድምፅ በመሆንና ድጋፍ በማቀበል፤ ችግሮቻቸውንና ብሦቶቻቸውን ለአሜሪካና ለዓለምአቀፍ ተቋማት እያሰሙ ለሕልፈታቸው ምክንያት የሆነው የጤና መሰናከል እስከገጠማቸው ዕለት አብረው ሲሠሩ ቆይተዋል።

እስከ ቅርብ ጊዜም ለረዥም ጊዜ የማዕከሉ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል።ለተጨማሪ መረጃ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ስለ ዶ/ር መምህርት ማይገነት ሺፈራው
please wait

No media source currently available

0:00 0:39:02 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG