በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዳግማዊት ኤልሳቤጥ ማረፍና የንግሥና ህይወት


የእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤ
የእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤ

በእንግሊዝ ለረጅም ዘመን ዙፋኑን ይዘው የቆዩት ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ትናንት ማለፋቸውን ተከትሎ፣ ንጉስ ቻርለስ ሳልሳዊ ዛሬ ዓርብ ስኮትላንድ ከሚገኘው መኖሪያቸው ወደ ለንደን ተመልሰዋል። ንግሥቲቱ ትናንት ያረፉትም እዚሁ ስኮትላንድ ውስጥ በሚገኝ ባልሞራል ካስል በተባለው መኖሪያቸው ነበር።

ንግሥቲቱ ሰሞኑን ጤና አልተሰማቸውም ነበር። በቅርብ የሃኪም ክትትል ውስጥም ነበሩ። የእንግሊዝ ባለሥልጣናትና ህዝቡም ስለ ንግሥቲቱ ጤንነት አብዝቶ ሲጨነቅ ሰንብቶ ነበር።

በ96 ዓመታቸው ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ለ70 ዓመታት ዙፋኑ ላይ ቆይተዋል።

የእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤጥ በ96 ዓመታቸው ማረፋቸው አስመልክቶ ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት መግቢያ ላይ የተሰቀለ ጹሁፍ እአአ ሐሙስ 9/8/2022
የእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤጥ በ96 ዓመታቸው ማረፋቸው አስመልክቶ ባኪንግሃም ቤተ መንግሥት መግቢያ ላይ የተሰቀለ ጹሁፍ እአአ ሐሙስ 9/8/2022

ንግሥት ኤልሳቤጥ በእንግሊዝ ንጉሣዊ አገዛዝ ታሪክ ለረጅም ዘመን የነገሱ ናቸው። ይህም ከቅም አያታቸው ከንግሥት ቪክቶሪያ ቀጥሎ ረጅሙ የንግሥና ዘመን መሆኑ ነው። ንግሥት ቪክቶሪያ ለ63 ዓመታት ነግሠዋል።

ለረጅም ዘመን በመንገሣቸውም፣ አብዛኛው የአሁኑ ትውልድ እንግሊዛዊ የሚያውቀው ንግሥት፣ እርሳቸውን ብቻ ነው።

ንግሥቲቱ የሃገራቸውና የግዛቶታቸው ምልክት ነበሩ። ንግሥት እንደሚሆኑ ከማወቃቸው ቀደም ብሎ ነበር የእንግሊዞችን ጥንካሬና ባህሪ መላበሳቸውን ያስመሰከሩት።

“አጭርም ይሁን ረጅም፣ መሉ ህይወቴን፣ እናንተንና የሁላችንም የሆነውን ታላቅ ንጉሣዊ ቤተሰብ ለማገልገል እንደማውል ቃል እገባለሁ” ብለዋል በጠዋቱ።

ንግሥት ኤልሳቤጥ ዙፋኑን ይቆናጠጣሉ ተብሎ አልተጠበቀም ነበር። ከ86 ዓመት በፊት ንጉሥ ኤድዋርድ ሰባተኛ፣ ዋሊስ ሲምፕሰን የተባለች ታዋቂ አሜሪካዊ ለማግባት ሲወስኑ ዙፋኑን ለቀዋል። ይህም በሃገሪቱ የነገሥታት ታሪክ ዋና አነጋጋሪ ከነበሩት ጉዳዮች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። የንግሥቲቱ አባት ንጉሥ ጆርጅ ስድስተኛ ዙፋኑን ሲረከቡ፣ ኤልሳቤጥን ለንግሥትነት ቅርብ አደረጋቸው።

ጆርጅ ስድስተኛ በሞት ሲለዩ፣ ንግሥት ኤልሳቤጥ በ25 ዓመታቸው ዙፋኑን ተረከቡ። ይህም የግሪኩን ልዑል ፊሊፕ ባገቡ በአምስተኛው ዓመት ነበር።

በሰባት አስርት ዓመታት ንግሥናቸው፣ ኅብረተሰብም ሆነ ቴክኖሎጂ ባልተጠበቀ ፍጥነት ሲያደግ አስተውለዋል። አዲስ ግኝቶችን በመልካም

ቢቀበሉም፣ ግዜ የማይሽራቸውና ነባር ሃሳቦችን ድንገት መተው አደገኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በእአአ 2014 የመጀመሪያ ትዊታቸውን ልከዋል።

የእንግሊዝን የነጻነት፣ እኩልነትና ዲሞክራሲ እሴቶች ከሚጋሩ ወገኖች ጋር ሃገራቸውን በመወከል በጋራ ቆመዋል። ይህን ከማይጋሩት ጋር ደግሞ፣ በክብር ልዩነታቸውን አሳይተዋል።

ከእርሳቸው ጋር መታየት ትልቅ ክብርን የመጎናጸፍ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል።

ንግሥቲቱ በሃገራቸው ከትችት ሙሉ ለሙሉ ነጻ ሆነው አልኖሩም።

ግራ ዘመሙ ወገን ንግሥቲቱን ዘመናዊው፣ ኒዮ ሊበራልና ዲሞክራሲያዊ በሆነው ዓለም ቦታ የሌለው ንጉሣዊ ተቋም ወኪል አድርገው ያይዋቸዋል። ለእንግሊዝ ታክስ ከፋዮችም ሸክም አድርገው ይቆጥሯቸዋል።

ፎቶ ፋይል፦ ልዕልት ዲያና ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ጋር ኬፕ ታውን እአአ 3//1997
ፎቶ ፋይል፦ ልዕልት ዲያና ከቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ጋር ኬፕ ታውን እአአ 3//1997

የልዕልት ዳያና ሞት ለነቃፊዎቻቸው ጥሩ አጋጣሚ ነበር። “ዘግይተውና እንደነገሩ ነው ሃዘናቸውን የገለጹት” ሲሉ ተችተዋቸዋል።

“አሁን ልነግራችሁ የምፈልገው፤ እንደ ንግስት፣ እንደ አያት፣ ከልቤ ነው የምለው፤ በቅድሚያ ለዳያና ያለኝን ክብር ራሴ መግለጽ እወዳለሁ። ልዮ የሆነችና የተለየ ሥጦታ ያላት ሰው ነበረች” ብለዋል እርሳቸው በበኩላቸው።

የልጅ ልጃቸው ልዑል ሃሪ፣ አሜሪካዊቷን ይፊልም ተዋናይ ሜጋን መርክል ሲያገባ፣ ንግሥቲቱና ንጉሣዊ ቤተሰቡ፣ ህዝባዊ፣ ቅይጥና ዓለማቀፋዊ መልክ ካለው የግዜው ሁኔታ ጋር አብረው እየሄዱ መስሎ ነበር።

ሃሪና ሜጋን ንጉሣዊ ቤተሰቡን በዘረኝነት በመክሰስ ራሳቸውን አራቁ።

የንግሥቲቱ ሁለተኛ ልጅ፣ ልዑል አንድሩ ከህጻናት ጋር ግንኑኘት በመፈጸም ከተከሰስ ግለሰብ ጋር ንኪኪ አላቸው በሚል ምርመራ መካሄዱ ለንግሥቲቱ አስቸጋሪ ወቅትን እንዲያሳልፉ አድርጓል።

የባለቤታቸው ልዑል ፊሊፕ አምና መሞት ግን የማይረሳ ምስል ለዓለም እንዲቀር አድርጓል። በኮቪድ-19 በተጠቃቸው ዓለም ንግሥቲቱ ብቻቸውን በቤተክስቲያን ሲያዝኑ ታይተዋል።

ንግሥቲቱ ከሁለት ቀናት በፊት፤ ማክሰኞ ለእርሳቸው 15ኛ የሆኑትን አዲሷን ጠቅላይ ምኒስትር ሊዝ ትረስ ሹመትን ስኮትላንድ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አጽድቀዋል። ጠቅላይ ምኒስትሯ የንግሥቲቱ የጤና ሁኔታ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ትናንት ጠዋት ተናግረው ነበር።

የእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤጥ፤ የበኩር ልጃቸው ልዑል ቻርልስ
የእንግሊዝ ንግሥት ዳግማዊት ኤልዛቤጥ፤ የበኩር ልጃቸው ልዑል ቻርልስ

ልጃቸው ልዑል ቻርለስ፤ አሁን ንጉሥ ቻርለስ፣ በቅርቡ በሚደረግ ሥነ-ስርዓት ዙፋኑን ይረከባሉ። ዛሬ ዓርብ ስኮትላንድ ከሚገኘው መኖሪያቸው ወደ ለንደን ተመልሰዋል። ሃዘን ላይ ላለው ህዝባቸውም ዛሬ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የንግሥና በዓላቸው ግን ትንሽ ግዜ እንደሚወስድ ይጠበቃል።

ዙፋኑን ከያዙበት እአአ 1952 ጀምሮ ንግሥት ኤልሳቤጥ ከመቶ በላይ ሃገሮችን ጎብኝተዋል። 150 የሚሆኑ ጎዞዎችን በዓለም ወዳሉ ግዛቶቻቸው አድርገዋል።

ንግሥቲቱ ኢትዮጵያንም ጎብኝተዋል።

የዳግማዊት ኤልሳቤጥ ማረፍና የንግሥና ህይወት
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:17 0:00

እአአ በ1965 ንግሥቲቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ ሞዓ አንበሳ፣ ዘእምነገደ ይሁዳ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥዩመ እግዚአብሄር፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸው ነበር።

ንጉሡና ንግሥቲቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን እየተዘዋወሩ ሲጎበኙ፣ በየሄዱበት ህዝቡ በሞቀ አቀባበል ተቀብሏቸዋል።

ንግሥቲቱ 112 የሚሁኑ የውጪ ሃገር መሪዎችን በቤተ መንግሥታቸው ተቀብለው አስተናግደዋል። ከነዚህ የዓለም መሪዎች ውስጥም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አንዱ ናቸው። በእአአ 1954 ኃይለ ስላሴ በበኪንግሃም ፓለስ ደማቅ መስተግዶ ተደርጎላቸዋል።

የንግሥት ኤልሳቤጥ ቀብር በመጪው ቀናት በአንዱ በዌስት ምኒስትር አቢ ይፈጸማል። ቀኑም “ብሔራዊ የሃዘን ቀን” ተብሎ ይሰየማል።

እንግሊዞቹ በሚሉት ንግሥቲቱን እንሰናበት፤

ንግሥቲቱ አርፈዋል፣

ንጉሱ ለዘላለም ይኑሩ!

XS
SM
MD
LG