በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ለኢትዮ ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት ድጋፍ ሰጠ


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ ከተማ

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተደረሰውን ስምምነት እንደሚደግፍ አስታወቀ፡፡


ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ “ለስምምነቱ ውጤታማነት በጋራ በመቆም ሚናችንን ለመወጣት ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም እናረጋግጣለን” ብሏል፡፡ መንግሥት ስምምነቱን “ውጥረቶችን በሚያረግብ እና ሀገሪቱን ለጉዳት በማያጋልጥ መንገድ” ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበትም ፓርቲዎቹ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ለኢትዮ ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት ድጋፍ ሰጠ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:24 0:00

ምክር ቤቱ ትናንት ባደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የታደሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የስምምነቱን ማዕቀፍ፣ ዝርዝር ይዘቱን እንዲሁም ከስምምነቱ ጋር ተያይዞ ባሉት እድሎችና ስጋቶች ላይ በዝርዝር መወያየታቸውን የጠቀሰው መግለጫው፣ ስምምነቱን ያለልዩነት ለመደገፍ መወሰናቸውንም አመልክቷል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲ አንድነት መድረክ ዋና ጸሐፊ አቶ ደስታ ዲንቃ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል ምክር ቤቱ ከውሳኔው ላይ የደረሰው፣ ከመግባቢያ ስምምነቱ በኋላ ያሉ ለውጦችን፣ የዲፕሎማሲ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


ወደ 60 ከሚጠጉ የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ውስጥ፣ በጉባዔው ታድመዋል ያሏቸው 49 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በመግባቢያ ሰነዱ ላይ ከመንግሥት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሃሳብ ማንፀባረቃቸውን ገልጸዋል፡፡

ለስምምነቱ ውጤታማነት በጋራ በመቆም ሚናችንን ለመወጣት ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም እናረጋግጣለን”

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የጋራ ምክር ቤት “ለስምምነቱ ውጤታማነት በጋራ በመቆም ሚናችንን ለመወጣት ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም እናረጋግጣለን” ያለ ሲሆን፣: መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና መላው ኅብረተሰብ የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ የሚል ጥሪም አቅርቧል፡፡ በሌላ በኩል በአፍሪካ ቀንድ ውጥረትን እያባባሰ መሆኑ እየተነገረ ያለው የመግባቢያ ሰነድ እንደሚያሳስባቸው የገለጹ አካላት አሉ፡፡


ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በእጅጉ አሳስቦኛል ያለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ ሁሉም ወገን እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርቧል፡፡


ኦነግ ዕሁድ ዕለት ባወጣው በዚህ መግለጫው፣ በእነዚህ “በስሜት የተሞሉ” ባላቸው ጊዜያት በሁለቱም በኩል ያሉት ስደተኞች እና ሲቪል ዜጎች ሊጠበቁ ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡


ከዚህ ቀደምም “በነዚህ ሀገሮች መካከል የተከሰቱ ተመሳሳይ ክስተቶች በኦሮሞ ስደተኞች እና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ዘላቂ የሆነ ጉዳት አድርሰዋል” ያለው ኦነግ፣ “የፖለቲካ ውጥረት በበዛበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት፣ በሶማሊያ የሚኖሩ የኦሮሞ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እንድትከላከሉ እንማፀናለን” የሚል መልዕክት ለሶማሊያ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስተላልፏል። ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ኦነግ ጠይቋል፡፡


በተያያዘ፣ የሠነዱ መፈረም የፈጠረው ውጥረት በማኅበረሰቦች መካከል መካረር እንዳያስከትልና በተለይም የስደተኞች ደኅንነት እንደሚያሠጋው የኦሮሞ ውርስ አመራርና ተሟጋች ማኅበር የሚባል ዋና ፅህፈት ቤቱ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ቡድንም ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።


በእንግሊዝኛ ስሙ መጠሪያ ምኅፃር ኦ-ላ (OLLAA) እየተባለ የሚጠራው ማኅበር፣ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ እየወጡ ያሉ ፀረ-ኦሮሞ ስሜቶችና በስደተኞች ላይ ያሉ የጥላቻ ንግግሮች በብርቱ እያሰጉት እንደሆነ አመልክቶ፣ የሶማሊላንድና የሶማሊያ መንግሥታት በከለላቸው ሥር ደኅንነትን ለጠየቁ ኦሮሞዎችና ሌሎችም ጥበቃ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።


አሜሪካን-ኢትዮጵያዊያን የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ የሚባል ቡድን በበኩሉ በኤክስ ገፁ ላይ፣ “በሶማሊያ ሕገመንግሥት፣ በአፍሪካ ኅብረት ቻርተርና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሪያዎች መሠረት ለሶማሊያ የግዛት አንድነት አስፈላጊነት አፅንዖት እንደሚሰጥ” እና “ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ” መሆኗን አስታውሶ ሀገሪቱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች “ቀጣናዊ ግጭቶችን መቀስቀስ ግድ የለሽነት ነው” ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG