በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ህይወት የቀጠፉ ያለፈው ሣምንት ጥቃቶች


በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ሣምንት በተሽከርካሪዎች ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

በክልሉ ምሥራቅ ሸዋ ዞን መተሃራ ከተማ አካባቢ ታህሳስ 19 በተፈፀመ ጥቃት በአንድ ተሸከርካሪ ውስጥ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ አሥር ሰዎች ደግሞ ታግተው መወሰዳቸውን ከሟቾች የአንዱ ቤተሰብ አባል ለአሜሪካ ድምፅ ተናግሯል።

ታጣቂዎቹ የገደሏቸውን ሰዎች አስከሬኖች ከተሸከርካሪው ጋር ማቃጠላቸውንም አስተያየት ሰጭው ገልጿል።

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሌመን ከተማ አቅራቢያ ታህሳስ 17 በተፈፀመ ጥቃት አንድ ሰው መገደሉንና ብዙ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸውን ተጎጂዎች አመልክተዋል።

ከመንግሥት አካላት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ካለፈው ሣምንት ጥቃቶች አንዱ በተፈፀመበት መተሃራ ከተማ አቅራቢያ በቁልቢ ገብርኤል ንግሥ ላይ ተገኝተው በመመለስ ላይ የነበሩ ስድስት ሰዎች በአንድ ተሸከርካሪ ውስጥ መገደላቸውን ለደኅንነቱ እንደሚሰጋ በመጥቀስ ስሙን እንዳንጠራ የጠየቀን ከተገደሉት የአንዱ ወንድም ተናግሯል።

ታህሳስ 19 በተፈፀመው በዚህ ጥቃት ከተገደሉት አምስቱ ከአዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ ለበዓሉ አብረው ተጉዘው ሲመለሱ ከነበሩ 18 የአንድ ሰፈር ወጣቶች መካከል መሆናቸውንና አንዱ ደግሞ ከቁልቢ አካባቢ ከቡድኑ ጋር ሲመጣ የነበረ ታዳጊ እንደነበረ መረጃ ሰጭው ገልጿል።

ወደ ቁልቢ ለመሄድ ከአቃቂ ታኅሳስ 16 መነሳታቸውን ጠቅሶ፣ “ወደ ወለንጪቲ መዳረሻ አካባቢ ጋቢና ከነበሩ ሦስት ሰዎች ላይ ታጣቂዎች ስልካቸውን እና 30 ሺህ ብር ተቀብለዋቸው አሳለፏቸው። ሽፍቶች ይመስሉኛል” ብሏል።

ታኅሣስ 19 አንግሠው ሲመለሱ “መተሃራ መግቢያ ኬላ አካባቢ ሲደርሱ የእኔ ወንድም የቡድን ተጓዦቹ ያሉበትን መኪና እያሽከረከረ ሲመጣ እንጨት አጋድመው መንገድ ዘጉበት። ከዛ መጀመሪያ እሱን ራሱ ላይ መቱትና ገደሉት። ቀጥሎም ጋቢና ውስጥ የነበሩትን ሁለት ሰዎችና ከኋላ ከነበሩት ሦስት ገደሉ” ብሏል። ቀጥለውም የተቀሩትን ከመኪናው እንዲወርዱ ካደረጉ በኋላ ሟቾቹን ከነመኪናው ማቃጠላቸውን፣ አሥር ሰዎችን አፍነው መውሰዳቸውን ተናግሯል።

በተሸከርካሪው ውስጥ ከነበሩት ውስጥ ጉዳት የደረሰባትን አንዲት ሴትና ከጠላፊዎቹ ጋር እኩል መጓዝ ያልቻሉ ሌሎች ሁለት ሴቶችን ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ያደረሱበት ላይ ትተዋቸው መሄዳቸውንና ሦስቱ ሴቶች ወደ ቤታቸው መመለሳቸውንም ገልጿል። መረጃውን ያገኘውም ከነዚሁ ተመላሾች መሆኑን የገለፀው የተጎጂ ቤተሰብ አባል ከቃጠሎ የተረፈውን የሟቾቹን አስከሬን ለማምጣት “በማግስቱ ግድያው ወደ ተፈፀመበት ስፍራ ሄደን ነበር፤ ነገር ግን እዚያው አካባቢ መቀበራቸውን መከላከያዎች ነገሩን። የተቀበሩበትን ስናይ በቃጠሎው ብዛት ምክንያት የሚታይ የአካል ክፍል የላቸውም” ብሏል። መከላከያዎችም “አመድ ሆኗል፤ ምኑን ትወስዳላችሁ? የግድ ከፈለጋችሁ ደግሞ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ አምጡ ሲሉን ተመልሰን መጣን” ብሏል።

ወንድሙን ጨምሮ አምስቱ ሟቾች የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች እንደሆኑና አካባቢው በለቅሶ ላይ መሆኑንም አስረድቷል።

ሌላው ባለፈው ሣምንት ጥቃት የተፈፀበት የክልሉ አካባቢ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሲሆን በዞኑ የቀርሳ ማሊማ ወረዳ ሌመን ከተማ ራቅ ባለ ሥፍራ ታህሳስ 17/2016 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡30 በኋላ ታጣቂዎች በአሥሮች የሚቆጠሩ ተሸከርካሪዎችን አስቁመው ከዘረፉ በኋላ እንዳቃጠሏቸው ከተጎጂዎች አንዱ ተናግሯል። ለማምለጥ የሞከረ አንድ ሾፌር ደግሞ መገደሉን ማንነቱ እንዳይጠቀስ የጠየቀው እማኝ ገልጿል።

ታጣቂዎቹ “ፀጉራቸው ትብትብና ጨብራራ ጎፈሬ” እንደሆነ” ጠቁሞ የእሱን ጨምሮ ያስቆሟቸው 13 የተለያየ ዓይነት ተሸከርካሪዎች ውስጥ የነበሩ ተሣፋሪዎችንና አሽከርካሪዎችን አስወርደው “ስልክና ገንዘባችንን ከተቀበሉን በኋላ፣ አንድ ግቢ ውስጥ ሰብስበውን እያየን መኪኖቹ ላይ ነዳጅ አርከፍክፈው አቃጠሏቸው” ብሏል።

ሌላ አሽከርካሪ ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበትም ተናግሯል። በአንድ ቦታ ላይ ከተቃጠሉት 13 መኪኖች ጋር ባጠቃላይ 28 መኪኖች መቃጠላቸውን ገልጿል።

ተሸከርካሪ ከተቃጠለባቸው አንዱ በዕለቱ በሥፍራው እንዳልነበረ ግለፆ በማግስቱ ወደ አካባቢው ሄዶ መኪናው መቃጠሉን እንዳረጋገጠ አመልክቷል።

የአካባቢውን ፖሊስ ለማናገር ስሞክር “ጥቃቱን ያደረሱት የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው፤ ኢንሹራንስ ካለህ የማስረጃ ደብዳቤ እንፅፍልሃለን አሉኝ፤ እኔ ግን ከ3ኛ ወገን ውጭ ለመኪናው ኢንሹራንስ አልገባሁም” ብሏል።

በመሰል ጥቃቶች በተደጋጋሚ የሚጠረጠረውና የሚከሰሰው የኦሮሞ ነፃነት ጦር የሚቀርቡበትን ውንጀላዎች እንደሚያስተባብል ይታወቃል። በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ሣምንት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች በተመለከተ ከኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮና ከክልሉ ፖሊስ፣ እንዲሁም ከፌዴራል ፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረግናቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች የባለሥልጣናቱ ስልኮች ባለመነሳታቸው ሊሳኩ አልቻሉም።

ስለተፈፀሙት ጥቃቶች የሚወጡ መረጃዎችን እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምርመራ እንደሚደረግ ነግሮናል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG