በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባለፉት ስድስት ወራት ቁጥራቸው የበዛ የዐማራ ተወላጆች እንደተገደሉ የፍጅት መከላከል ድርጅቱ ገለጸ


ባለፉት ስድስት ወራት ቁጥራቸው የበዛ የዐማራ ተወላጆች እንደተገደሉ የፍጅት መከላከል ድርጅቱ ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:23:25 0:00

ባለፉት ስድስት ወራት ቁጥራቸው የበዛ የዐማራ ተወላጆች እንደተገደሉ የፍጅት መከላከል ድርጅቱ ገለጸ

መሐመድ ሰዒድ ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ ነው። ከአጎቱ እና ከቤተሰቦቹ ጋር በምዕራብ ወለጋ፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌም ይኖር ነበር። ከአስር አመት በፊት ትዳር ከያዘ እና ልጅ ከወለደ በኃላ ደግሞ፣ ከቶሌ ቀበሌ በሁለት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ፣ በካማሺ ዞን፣ ኢቩንጉዲ ቀበሌ ውስጥ ይኖር ነበር።

ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ቶሌ ቀበሌ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ኢቩንጉዱ ቀበሌ በአንድ ቀን በደረሰ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ግን ሰባት የቤተሰቡን አባላት እና ቤት ንብረቱን እንዳጣ ይገልፃል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቶሌው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 338 መሆኑን አስታውቆ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የአማራ ማክበር በበኩሉ በጥቃቱ 503 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን አመልክቷል። መሐመድ በቤተሰቦቹ ላይ ጥቃት አደረሱ የሚላቸው ማህበረሰቡ ሸኔ እያለ የሚጠራቸው እና፣ እራሳቸውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ሲሆኑ፣ ቡድኑ ታጣቂዎቹ ይህን አይነት ጥቃት ላይ እንደማይፈፅሙ በተድጋጋሚ በመግለፅ በምትኩ መንግስትን ተጠያቂ ያደርጋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች “የትግራዩ ጦርነት የኦሮምያውን ግጭቶች እንዳይታዩ አድርጓል” በሚል ባወጣው ሪፖርት በሐምሌ ወር ባወጣው ሪፖርት፣ በሰኔ ወር ውስጥ በምዕራብ ኦሮሚያ ቶሌ በተባለች መንደር በመቶዎች የተቆጠሩ፣ አብዛኞቹም የአማራ ብሄር ተወላጆች የሆኑ ንጹሃን በታጣቂዎች መጨፍጨፋቸውን አስታውቋል። የመብት ተሟጋች ድርጅቱ፣ “የአካባቢው ባለሥልጣናት ታጣቂው ቡድን ተጠያቂው ነው” ቢሉም ታጣቂው ቡድን በበኩሉ “የፈጸምኩት ነገር የለም” ሲል ውንጀላውን አስተባብሎ በፊናው የመንግስት ደጋፊ ሚሊሻዎችን ተጠያቂ አድርጓል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱ በታጣቂዎች እንደተፈፀመ ገልፀው፣ መንግሥት ከጥቃት እንዳልተከላከለላቸው ተናግረዋል።

ጥቃቱ ከመፈፀሙ በፊት በነበሩት ሁለት ዓመታት ሰዎች እየታገቱ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይጠየቁ እንደነበር የሚያስታውሰው መሐመድ፣ ለመንግስት ሀላፊዎች እና የፀጥታ በተደጋጋሚ ያቀረቡት አቤቱታ ሰሚ በማጣቱ ቤተሰቦቹን እንዲያጣ እና እንዲሰደድ ምክንያት መሆኑን ይገልፃል።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው መሐመድ አሁን የሚኖረው፣ በተመሳሳይ ጥቃቶች ከተፈናቀሉ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ጋር በደቡብ ወሎ ዞን ቃሎ ወረዳ ውስጥ ነው። እሱ እንደሚለው ከጥቅምት 15፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ያደርግላቸው የነበረውን ድጋፍ በማቋረጡ እና መጠለያ ጣቢያዎቹን በመዝጋቱ፣ በአንድ ወቅት ቤተሰባቸውን ያስዳድሩ የነበሩ ሰዎች፣ አሁን የሰው እጅ እያዩ ለመኖር ተገደዋል።

መሐመድ ባለፉት ጥቂት አመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በደረሱ ጥቃቶች አንድ እና ከዛ በላይ የቤተሰባቸውን አባላት ከአጡ የአማራ ተወላጆች መካከል አንዱ ነው።

በኢትዮጵያ በልዩ ልዩ አካባቢዎች በሚኖሩ የዐማራ ተወላጆች ላይ፣ በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች እየደረሱ ናቸው በተባሉ ጥቃቶች፣ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ፣ 11ሺሕ ሰዎች እንደተገደሉና ከ100ሺሕ በላይ ሰዎች ደግሞ እንደታሰሩ፣ “የዘር ፍጅት ቅድመ መከላከል በኢትዮጵያ” የተሰኘ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት አስታውቋል።

በተለይ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፣ ለአመታት ታጣቂዎች በአማራ ተወላጆች ላይ ያደርሱት የነበረው ጥቃት፣ በመንግስት ኃይሎችም ታግዞ በክልሉም ላይ ጭምር መቀጠሉንም አመልክቷል።

ለሁለት ዓመት በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሔደው ጦርነት በስምምነት ከቆመ በኋላ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በፋኖ ታጣቂ መካከል እየተካሔደ ባለው ግጭት ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ፣ ከፌዴራልም ኾነ ከክልሉ መንግሥት እስከ አሁን የተገለጸ ቁጥር ባይኖርም፣ ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ በዐማራ ክልል ብቻ 764 ሰዎች እንደታሰሩ መርማሪ ቦርዱ ባለፈው ወር አስታውቆ ነበር።

ድርጅቱ ባአወጣው ሪፖርት ላይ፣ ከፌዴራልም ኾነ ከዐማራ ክልል መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም፣ ቀጥተኛ ምላሽ አላገኘንም።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በዐማራ ክልል እየተካሔደ ባለው ግጭት፤ በዐማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን የእስር ዘመቻ እና ሌሎችም የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በተለያዩ ጊዜያት አውግዟል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት በሚያወጧቸው ሪፖርቶች፣ በዐማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንደሚያሳስቧቸው ገልጸዋል።

(ስመኝሽ የቆየ የተቋሙን ዳይሬክተር ዶ/ር ሰናይት ደረጀን አነጋግራ ያሰናዳችውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።)

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG