በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ ክልል ዞኖች የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉ ተገለጸ


በኦሮሚያ ክልል ዞኖች የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:57 0:00

በኦሮሚያ ክልል ዞኖች የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉ ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ እና በሆሮ ጉድሩ ዞኖች፣ እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎች የተኩስ ልውውጥ መቀጠሉን፣ ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ፡፡

በፌዴራል መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል፣ በታንዛኒያ የቅድመ ድርድር ንግግር መጀመሩ ተስፋን ሰጥቷቸው እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ የአካባቢያቸው ጸጥታዊ ኹኔታ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ ነዋሪ መኾናቸውን ገልጸው ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን አንድ ግለሰብ፤ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል፣ የቅድመ ድርድር ንግግር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካሔደ ወዲህ፣ የቤተሰቦቻቸው ቤት መቃጠሉን ገልጸዋል።

በሰላም ድርድሩ ተስፋ እንደነበራቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፤ “በሰላም ድርድር ጥያቄው፥ ችግራችን ይፈታልሰላም እናገኛለን ብለን ስንደሰት ነበር። ኾኖም፣ አኹንም በአካባቢያችን እየታየ ያለው ነገር በጣም አስከፊ ነው። ባለፈው ሳምንት ውስጥ እንኳን፣ የቤተሰቦቻችንን ቤት ጨምሮ በሰሜን ሸዋ ያያ ጉላሌ ወረዳ ጎዳ ጃባ ቀበሌ ሰባት ቤቶች ተቃጥለዋል።”

እኚኹ ነዋሪ፣ ቤቶቹ የተቃጠሉት፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ነው፤ ሲሉ ይከሣሉ። ምክኒያቱ ደግሞ፣ መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ የሚጠራውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎችን ትደብቃላችኹ፤ በሚል እንደኾነ አስረድተዋል።

መኖሪያቸውን በቨርጂኒያ ያደረጉት የታጣቂዎቹ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በትዊተር ገጻቸው አከታትለው በአሠፈሯቸው መረጃዎች፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋራ ውጊያ መግጠማቸውንና የመንግሥት ወታደሮችን መግደላቸውን አስታውቀዋል።

በጉዳዩ ላይ ከፌደራል መንግሥትም ኾነ ከኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁን በቄለም ወለጋ ዞን ነዋሪ መኾናቸውን የገለፁ ሌላው ነዋሪ፤ የሰላም ድርድሩ ከተጀመረ ወዲህ፣ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም፣ በቀጣይነቱ ላይ ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።

“ሕዝቡ የሰላም ድርድሩን በተስፋ እየተጠባበቀ ይገኛል። በተለይ ይህ ዞን፣ በሰላም መደፍረስ ምክንያት እጅግ የተጎዳ ነው። አሁንም የሚታዩት ግጭቶች አሳሳቢ ናቸው።” ብለዋል።

በአምቦ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ሰሎሞን ተፈራ፣ የተጀመረው የሰላም ሒደት ይቀጥል ዘንድ፣ በሰላም ዕጦት በችግር ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ግፊት ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

አኹን ግጭት እንዳለባቸው ከተነገሩት አካባቢዎች አንዱ በኾነው ምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደ በረት አካባቢ የተወለዱትና ስለአካባቢ መረጃ እንዳላቸው የገለጹልን አቶ ደስታ ዲንቃ፣ በዞኑ ግጭት መቀጠሉን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA)፣ ባለፈው ዐርብ በአወጣው ሪፖርት፣ በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የጸጥታ ችግር መቀጠሉን ጠቁሟል። ይህም ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት እንዳይኖር እንቅፋት መፍጠሩን አመልክቷል።

ይህም ኾኖ፣ መንግሥት እና አጋሮች፣ በአካባቢው የሚገኘውን እያንዳንዱን የሰላም ዕድል፣ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ለመድረስ እየተጠቀሙበት እንደኾነ የማስተባበርያ ቢሮው ገልጿል።

XS
SM
MD
LG