በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራዊውን ስደተኛ በመግደል ወንጀል የተከሰሰው እሥራኤላዊ ፖሊስ ነፃ ተባለ


ፋይል- የእሥራኤል ፖሊስ በፓኪስታናዊ ተጠርጣሪ ጥቅምት 19, 2015.
ፋይል- የእሥራኤል ፖሊስ በፓኪስታናዊ ተጠርጣሪ ጥቅምት 19, 2015.

አንድ የእሥራኤል ፍርድ ቤት፣ ባለፈው ጥቅምት ወር በደቡባዊ እሥራኤል በርሸባ ከተማ በሚገኝ አውቶቡስ ጣቢያ አካባቢ በአንድ ኤርትራዊ ስደተኛ ላይ ግድያ ከፈጸሙ ቡድኖች ጋር ተባባሪ ነው የተባለውን የእስር ቤት ሠራተኛ በነፃ መልቀቁ ተነገረ። ኤርትራዊው ሀብቶም ዘርኦም የተገደለው ከሌላ ነፍሰ-ገዳይ ጋር በተምታታ የማንነት ጥያቄ ምክንያት መሆኑንም ዘገባው ይገልጻል።

የእሥራኤል መከላከያ ኃይል አባል የነበረውና የ19 ዓመቱ ዑመሪ ለቪ በሽብርተኞች ይገደላል። ገዳዩን ለማጣራት በተደረገ ክትትል ሀብቶም በስህተት ይያዝና በፖሊሶች ይደበደባል፣ በኋላም አንድ የእሥራኤል ፖሊስ ተኩሶ ይገድለዋል።

የእሥራኤል እስር ቤት ተቀጣሪ የሆነው ሃነንያ ሻባት የተባለው ፖሊስ፣ አላስፈላጊና ከመጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በመውሰዱና ለኤርትራዊው ሀብቶም ሞት ምክንያት ተደርጎ ይወነጀላል። ይሁን እንጂ ከቀረበበት የወንጀል ክስ ነፃ ተብሏል።ጠበቃው ዳን ግሩቭስ “ደንበኛዬና ሌሎቹም የእስር ቤቱ ሠራተኞች፣ በአውቶቡስ ማቆሚያው ሰፈር ሲያልፉ ረብሻውን ለማረጋጋት ከመሞከር ያለፈ ምንም የፈጸሙት ወንጀል የለም” ሲሉም ተከላክለዋል። ይህንኑ ለቪኦኤ እንዲህ ሲሉ ይገልጣሉ።

“ፍርድቤቱ የቀረቡለትን መረጃዎች በጥንቃቄ መርምሮ ሲያበቃ ትክክለኛውን ብይን ሰጥቷል። መረጃዎቹም ሲታዩ፣ ከአውቶቡስ ጣቢያው ውጪ እየነዳ እንደነበር ሁኔታው በግልጽ ያስረዳል።ምንም እንኳ ሥራቸው ባይሆንና ባይመለከታቸውም መኪናቸውን አቁመው ወደ ውስጥ በመግባት ለመርዳት የሞከሩና ምንም ጦር መሣሪያም ያልታጠቁ ነበሩ።”

ተከላካይ ጠበቃው ግሩቭስ ደንበኛቸው ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ ከሥራ መታገዱን ገልጸው፣ አሁን ግን ወደ ሥራ ገበታው በመመለስ ሕይወቱን መምራት ይቀጥላል ብለዋል።

አሁን፣ የሀብቶም ዘርኦምን ቤተሰብ የሚወከሉት ጠበቃ ሊሞር ሉጋሲ “ሽብርተኞች አውቶቡስ ውስጥ ሲገቡ ቁጥጥር ባለመደረጉ፣ ቸልተኛነት ነው” በማለት የሴኩሪቲውን ጉዳይ በሚመራው ኩባንያ ላይ ክስ መስርተዋል። ክሱ በተጨማሪም፣ ለሀብቶም መሬት ላይ ተጥሎ መደብደብና መሞት ምክንያት የሆነውን ረብሻ ማስቆም በተሳነው የፖሊስ ክፍል ላይም ውንጀላ አድርጓል። ጠበቃ ሊሞር ለቪኦኤ እንዲህ ነበር ያብራሩት።

“ሀብቶም በቦታው ሲደርስ ምንም ዓይነት አስፈሪ ሁኔታ አልነበረም። ጥይት የተገደለው ሀብቶም፣ ትጥቅም አልያዘምና ማንም ሰው ሊፈራ ወይም ስጋት ሊያድርበት የሚችል የለም። አደገኛ ነው፣ እኛም ተገቢ እርምጃ ነው የወሰድንው ማለት ከቶ አይቻልም።”

ሀብቶም በጥቅምት 18 ቀን ወደ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በመሄድ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኘ በኋላ፣ ኑሮውን እሥረኤል ውስጥ እንዲቀጥል ተፈቅዶለታል ብለዋል ጠበቆቹ።

ቀደም ሲል በርሼባ ወረዳ ፍርድ ቤት የተመሰረተው ክስ፣ የብሔራዊው ኢንሻንስ ኩባንያ መሥሪያ ቤት፤ ሀብቶምን “የሽብርተኛነት ሰለባ” የሚል እውቅና እንዲሰጠውና፣ የ3 ሚሊዮን አዲሱ የእሥራኤል ሼክል ($780,000 መሆኑ ነው) ካሳ እንዲከፈለውም ጠይቋል።

ሀብቶም ወደ እሥረኤል የገባው በህገ-ወጥ መንገድ ነው በሚል ጥያቄው ውድቅ መሆኑን የእሥረኤል ራድዮ ቢዘግብም፣ “ከመንግሥት ጋር ቀጣይ ውይይት ይዘናል” ይላሉ ጠበቆቹ። “ለቤተሰቡ ካሳው እንዲከፈል መንግሥትን ጠይቀናል፣ እስካሁን ግን መልስ አላገኘንም፣ በወር ጊዜ መልስ ይሰጡናል ብለን እንጠብቃለን” ጠበቃዎቹ አክለው ገልጸዋል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።

ኤርትራዊውን ስደተኛ በመግደል ወንጀል የተከሰሰው እሥራኤላዊ ፖሊስ ነፃ ተባለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:20 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG