በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም አቀፍ ፍ/ቤት የደቡብ አፍሪካን አቤቱታ ውድቅ እንዲያደርግ እስራኤል ጠየቀች


ሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ሄግ፣ ኔዘርላንድስ እአአ የካቲት 2/2024.
ሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ሄግ፣ ኔዘርላንድስ እአአ የካቲት 2/2024.

ለፍልስጥኤም እንደሀገር ዕውቅና መስጠት "ካሁን ቀደም ባልታየ ደረጃ ስለደረሰው ሽብርተኝነት ትልቅ ሽልማት መስጠት ይሆናል" ሲሉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ አሳሰቡ።

ኒታንያሁ ዛሬ ዓርብ ማለዳ በኤክስ ማሕበራዊ መገናኛ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ጋር ከተነጋገሩ እና የካቢኔ ስብሰባ ካደረጉ በኋላ መሆኑ ታውቋል።

ዩናይትድ ስቴትስ እና የአረብ ሀገራት አጋሮቿ በመካከለኛው ምስራቅ ለቀጠለው ግጭት እስራኤል እና ፍልስጥኤም ሁለት ሀገሮች ሆነው ጎን ለጎን የሚኖሩበት መፍትሔ እንዲሰጥ የሚለውን ሐሳብ ለመግፋት ዕቅድ እንዳላቸው ዘ ዋሽንግተን ፖስት ያወጣውን ዘገባም ተከትሎ ነው።

"እስራኤል ከፍልስጥኤማውያን ጋር ለዘላቄታው ስለምትከተለው ዕቅድ ዓለም አቀፍ ጫና እንዲደረግባት ፈጽሞ አትፈቅድም" ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከፍልስጥኤማውያኑ ጋር ማናቸውም ስምምነት ላይ ሊደረስ የሚችለው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቀጥታ በመደራደር ብቻ ነው" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በራፋህ የፍልስጥኤማውያንን መብት ለማስከበር ተጨማሪ አስቸኳይ ማዘዣዎች እንዲያወጣ ደቡብ አፍሪካ ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ እንዲያደርግ እስራኤል ጠይቃለች።

ፍርድ ቤቱ ትናንት ሐሙስ ይፋ ባደረጋቸው ሰነዶች መሠረት ፍርድ ቤቱ ባለፈው ወር ያወጣቸው ማዘዣዎች በአጠቃላይ ጋዛ ውስጥ የሚካሂዱትን ግጭቶች የሚሸፍን በመሆኑ ተጨማሪ እርምጃ አያስፈልግም በማለት እስራኤል ተከራክራለች።

ደቡብ አፍሪካ ማክሰኞ ዕለት ለዓለሙ ፍርድ ቤት ባቀረበችው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ በጥር ወር ማዘዣውን ካወጣ ወዲህ የተለወጠ ሁኔታ መኖሩን ማለትም ኔታንያሁ ራፋህ ላይ ጥቃት እንዲከፈት ማዘዛቸውን አመልክታለች።

የረጅም ጊዜ የፍልስጥኤማውያን ትግል ደጋፊ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ "የእስራኤል የጦር ሠራዊት ጋዛ ውስጥ የዘር ማጥፋት እየፈጸመ ነው' በማለት መክሰሷን ተከትሎ እስራኤል የፍልስጥ ኤማዊያን ሲቪሎችን ህይወት እንዳይጠፋ የተቻላትን ሁሉ እንድታደርግ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል። እስራኤል የዘር ማጥፋት ውንጀላውን ታስተባብላለች።

ደቡብ አፍሪካ ለቀረበችው አዲስ አቤቱታ የዓለሙ ፍርድ ቤት መቼ ውሳኔ እንደሚሰጥ አይታወቅም።

የእስራኤል የምድር ጦር ራፋህ ላይ ጥቃት እንደሚጀምር በሚጠበቅበት ባሁኑ ወቅት አውስትሬሊያ፥ ካናዳ እና ኒውዚላንድ ስለ ሲቪሎቹ ደህንነት በዓለም አቀፍ አካላት የሚቀርበውን ስጋት ተቀላቅለዋል።

ኔታንያሁ ረቡዕ በሰጡት ቃል ራፋህ ላይ ጥቃቱ መቼ እንደሚጀመር ሳይገልጹ የጦር ሠራዊታችን ጋዛ ውስጥ የሀማስን ታጣቂዎች መውጋቱን ይቀጥላል ብለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG