“ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ” ለኦሮሞ ተቃውሞ መልስ ግድያና እስራት በኢትዮጵያ በሚል ርእስ የሚጀምረው የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት የኢትዮጵያ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከሕዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ ኦሮሚያ ክልል ተስፋፍቶ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ተሳታፊዎች ላይ ከመጠን ያለፈ እና እስከ መግደል የሚያደርስ ሃይል ተጠቅሟል፡፡
400 የሚገመቱ ሰዎች ተገድለዋል፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በዐስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል፤ እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ እና ምናልባትም ከዚህ ቁጥር የሚልቁ ሰዎች ደግሞ ተገደው የተወሰዱበት አልተወቀም ይላል- ሪፖርቱ።
የሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሊፍኮው ስለ ሪፖርቱ ይዘት ለአሜሪካ ድምጽ ሲናገሩ፤ ተቃውሞው የጀመረው በሕዳር ወር መግቢያ 2008 ዓ.ም መሆኑን ገልጸው የተቃውሞው መነሻ ደግሞ የመንግስት ባለስልጣናት በጊንጪ የሚገኝ አንድ ደን እና የእግር ኳስ ሜዳን ለኢንቨስትመንት ልማት ለማጽዳት መወሰናቸው እንደሆን ያስረዳሉ።
በዚህ አካባቢ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎም ቢያንስ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በ17ቱንም ዞኖች ውስጥ ባሉ የተለያዩ 400 አካባቢዎች ተቃውሞው እንዲዛመት መነሻ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
“ላለፉት ሰባት ወራት 500 እና ከዚያ በላይ የሆኖ ተቃውሞዎችን ሙሉ ይዘት ተከታትለን መዝግበናል። ከነዚህ ተቃውሞዎች ደግሞ አብዛኞቹ ፍጹም ሰላማዊ ነበሩ። ነገር ግን የጸጥታ ኃይሎች ውሃ እና የጎማ ጥይትን ጨምሮ የመግደል ደረጃ የማያደርሱ ነገሮችን ከመጠቅም ይልቅ፤ በቀጥታ ወደ ሰዎች መተኮስን ጨምሮ እስከ መግደል የሚያደርስ ያልተመጣጠን ሃይል ተጠቅመዋል። እኛም ከተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ባገኘነው መረጃና ባደረግነው ተደጋጋሚ ማጣራት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሰልፍኞቹ ላይ ፍፁም ተመጣጣኝ ያልሆን ኃይል ተጠቅመዋል” ይላሉ ሌስሊ ሊፍኮው።
ሪፖርቱ የተጠናቀርው ከ125 በላይ ከሆኑ የአይን እማኞች እንደሆነ የሚናገሩት ሌስሊ ሊፍኮው፤ ከተጠቂዎች እና ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ቃለምልልስም ተካቶበታል ብለዋል። በተጨማሪም ከሕዳር እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ውስጥ በኦሮሞ ሰልፈኞች ላይ የተፈጸመውን እጅግ በጣም ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስተቶችን በመመዝገብ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።
ሪፖርቱ ስለታሰሩ ሰዎች በሚዘረዝርበት ክፍልም፤ የፀጥታ ሃይሎች በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ተደማጭነት አላቸው ተብለው የተገመቱ ሰዎችን ለመለየትና ለማሰር ትኩረት የሚያደርጉባቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ለአብነት ሙዚቀኞች፣ መምህራን፣ የተቃዋሚ አመራሮች እና ሌሎች ማኅበረሰቡን ለቀጣይ አመጽ የማነሳሳት አቅም አላቸው ብለው የገመቷቸውን ሰዎችን ሰብስበው አስረዋል ይላል። በጸጥታ ሃይሎች ከታሰሩት እና ከታገደሉት በርካታዎቹ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንደሆኑም ይዘረዝራል፡፡የፀጥታ ሃይሎች ያገቷቸውን ሰዎች ያሰቃያሉ አሊያም ያልተገባ አያያዝ ይፈጽሙባቸዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።