በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በጎንደር የወደመው ንብረት ዝርዝር ውጤት በአንድ ብሔር ላይ የተነጣጠረ ጥቃት መኖሩን አያሳይም” አቶ ንጉሱ ጥላሁን


የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን
የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን

ሐምሌ አምስት ቀን ጀምሮ በተከታታይ ባሉት ሶስት ቀናት በጎንደር ከተማ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በጎንደርና በደባርቅ በደረሰው ንብረት ውድመት በተደረገው ማጣራት በአጠቃላይ በጎንደር የ139 በደባርቅ ደግሞ የሦስት ኢትዮጵያውያን ንብረት በተለያየ ደረጃ መውደሙን የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናገሩ። ይህንን ቁጥር ዘርዝረው በማብራራት ወደ አንድ ብሔር ያደላ ጥቃት እንዳልተፈፀመ ተናግረዋል።

ሐምሌ አምስት ቀን ጀምሮ በተከታታይ ባሉት ሶስት ቀናት በጎንደር ከተማ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በጎንደርና በደባርቅ የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ በርካታ ሆቴሎችና መጠኑ ለጊዜው ያልታወቀ ንብረት በቃጠሎ መውደሙንና መዘረፉን መዘገቡ ይታወሳል።

ይህንኑ በተመለከተም በወቅቱ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ጥያቄ አቅርበንላቸው ሁኔታው በመጣራት ላይ እንደሆነም ገልፀው ነበር።

ድርጊቱ ከተፈፀም ሃያ ቀናትን ያስቆጠረ በመሆኑ ማጣራት የተደረገበት እንደሆነ ጠይቀናቸው፤ በተደረገው ማጣራት በአጠቃላይ የ16 ሰው ሕይወት ማለፉን፣ 16 ሰው መቁሰሉንና በአጠቃላይ የ139 ኢትዮጵያውያን ንብረት በተለያየ ደረጃ መውደሙን ተናግረዋል። ይህ ቁጥር ወደ አንድ ብሔር ያደላ ጥቃት ያሳይ እንደሆነ ተጠይቀው፤ ምንም እንኳን በስም እየጠሩ መዘርዘሩ ተገቢ ባይሆንም መሬት ላይ ያለው ሐቅ መታወቅ ስላለበት ዝርዝሩን ለመናገር እንደሚገደዱ ገልጸው ፤ ከጠፋው ንብረት ውስጥ የአማራ 85፣ የትግራይ 30 ቀሪው ደግሞ የሌሎች ብሔር ተወላጆች ንብረት መሆኑን የኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዳይሬክተሩ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል።

የአሜሪካ ድምፅ የኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁንን አነጋግሮ ያጠናከረውን ዘገባ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።

ቀጥተኛ መገናኛ


XS
SM
MD
LG