በአማራ እና በትግራይ ክልሎች አዋሳኞች የይገባኛል ጥያቄ ለሚነሣባቸው አካባቢዎች፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዘላቂ እልባት ለመስጠት በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ከትግራይ ክልል የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋራ ባደረጉት ውይይት፣ በአከራካሪ ቦታዎች ላይ የፌዴራሉ መንግሥት የጸጥታ ኀይሎች ብቻ እንደሚኖሩ ገልጸዋል። ከነዚኽ አካባቢዎች ተፈናቅለው በትግራይ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ በማንኛውም ሰዓት ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ከፈለጉ፣ መንግሥት ለማስፈጸም ዝግጁ እንደኾነም አበክረው ተናግረዋል።
ብሔራዊ ኮሚቴው፣ እስከ አሁን የተፈጸሙና ሊፈጸሙ ሲገባቸው የዘገዩ ጉዳዮችን መገምገሙን የዘገቡ መንግሥታዊ ብዙኀን መገናኛዎችም፣ ተፈናቃዮችን በአጭር ጊዜ ወደ ቀዬቸው ለመመለስ በሚቻልበት አግባብ ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሠራ የጋራ መተማመን ላይ እንደተደረሰ አስታውቀዋል።
በዚኹ የግምገማ መድረክ፣ የማንነት እና የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው አካባቢዎች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፣ በአፋጣኝ እና በዘላቂነት ሊፈቱ እንደሚገባ ስምምነት ላይ እንደተደረሰም በዘገባዎቹ ላይ ተመልክቷል።
ግምገማው የተካሔደው፥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዲሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንና የሁለቱ ክልሎች ርእሳነ መስተዳድሮች በተገኙበት እንደኾነ በዘገባዎቹ ተጠቅሷል፡፡
በጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን የብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ተስፋይ ንጉሥ፣ ችግሩን ለመፍታት ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት ገልጸዋል፡፡ የሁለቱ ክልሎች ወቅታዊ ኹኔታ ስለሚኖረው ተጽእኖ የተጠየቁት አቶ ተስፋይ፣ ለታቀደው ተግባር ፈተና እንደሚኾን አመልክተዋል፡፡
የኮሚቴውን መቋቋም “አበረታች” ሲሉ የገለጹት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና ሰብአዊ መብቶች መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ በአንጻሩ፣ ሁለቱ ክልሎች አሁን ባሉበት ኹኔታም፣ ብሔራዊ ኮሚቴው ሥራውን ማከናወን እንደሚችል እምነታቸውን አብራርተዋል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት፣ መንግሥት “አከራካሪ” ሲል ከሚገልጻቸው የትግራይ እና የአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያመለክታል፡፡
የትግራይ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ፣ በአማራ እና በኤርትራ ኀይሎች ተይዘዋል ካላቸው ስፍራዎች ተፈናቅለው በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ መኾኑን ገልጿል፡፡
ተፈናቃዮች ከቀጣዩ የክረምት ወቅት በፊት ሙሉ በሙሉ ወደቀዬአቸው መመለስ እንዳለባቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የአከራካሪ አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄዎች፣ በሕዝበ ውሳኔ እልባት እንደሚያገኙ፣ ከክልሉ የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋራ በነበረው ውይይት ላይ በድጋሚ አንሥተዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ኢንተለጀንስ ማኅበረሰብ በቅርቡ ባወጣው የፈረንጆቹ 2024 ዓመታዊ የስጋት ግምገማ ሪፖርት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ “ያልተፈቱ የግዛት ጉዳዮች ዳግም ግጭት እንዲቀሰቀስ ሊያደርጉ ይችላሉ፤” ሲል አስጠንቅቋል፡፡
መድረክ / ፎረም