በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራይ ክልል ተፈናቃይ ሰልፈኞች ሰብአዊ ድጋፉ እንዲቀጥልና ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ጠየቁ


የትግራይ ክልል ተፈናቃይ ሰልፈኞች ሰብአዊ ድጋፉ እንዲቀጥልና ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:56 0:00

የትግራይ ክልል ተፈናቃይ ሰልፈኞች ሰብአዊ ድጋፉ እንዲቀጥልና ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ጠየቁ

“በፕሪቶሪያው ስምምነት ችግሩ በፖለቲካዊ መንገድ እንዲፈታ እንሠራለን”- ጊዜያዊ አስተዳደሩ

በትግራይ ክልል ስድስት ከተሞች የሚገኙ ተፈናቃዮች፣ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እንዲችሉ የጠየቁበትን ሰላማዊ ሰልፍ አካሔዱ፡፡

ሰላማዊ ሰልፎቹ የተካሔዱባቸው ከተሞች፥ መቐለ፣ ዓዲ ግራት፣ ዓብዪ ዓዲ፣ ዓድዋ፣ ሽረ እንዳሥላሴ እና አኵስም ናቸው፡፡

ሰልፈኞቹ፥ የተቋረጠባቸው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀጥልና ይህም በአስቸኳይ እንዲተገብር፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል::

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፥ የተፈናቃዮቹን ጥያቄ ለመመለስ፣ በፕሪቶርያው ስምምነት መሠረት፣ ከፌዴራሉ መንግሥት ጋራ ተባብሮ እየሠራ መኾኑን፣ ለሰላማዊ ሰልፈኞቹ ገልጿል፡፡

የኢሮብ፣ የኩናማ፣ የምዕራብ ትግራይ፣ እንዲሁም የሰሜን ምዕራብ እና የደቡብ ትግራይ ወሰን አካባቢዎች ተፈናቃዮች፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በአካሔዱት ሰላማዊ ሰልፍ፥ የፕሪቶርያው ስምምነት በሙሉ ቃሉ እና በሙሉ መንፈሱ እንዲተገበር ጠይቀዋል፡፡

በመቐለ ከተማ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ፥ የኤርትራ ሠራዊት እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ውጪ ያሉ ኃይሎች፣ ከትግራይ ክልል ወሰኖች እንዲወጡና ይህንም ተከትሎ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ አመልክተዋል፡፡

ከኢሮብ ወረዳ መፈናቀላቸውን የተናገሩትና ከሰልፈኞቹ አንዱ የኾኑት አቶ ዑቑባይ ደስታ፣ በአሁኑ ጊዜ የኢሮብ ብሔረሰብ በመበታተን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ፣ ብሔረሰቡን ከጠቅላላ ጥፋት እንዲታደገው ጠይቀዋል፡፡

ሠርተን መኖር እንጂ፣ ተረጂ መኾን አንፈልግም፡፡ ቤታችን ናፍቆናል፤ ወደ ቀዬአችን መመለስ እፈልጋለን፤”

ከሑመራ ከተማ የተፈናቀሉት ሌላዋ ሰልፈኛ ወይዘሮ አጀብነሽ መለስ በበኩላቸው፣ “ሠርተን መኖር እንጂ፣ ተረጂ መኾን አንፈልግም፡፡ ቤታችን ናፍቆናል፤ ወደ ቀዬአችን መመለስ እፈልጋለን፤” ብለዋል፡፡

ተፈናቃይ ሰልፈኞቹ፣ በመቐለ ከተማ በሚገኙ ሰብአዊ ረድኤት በሚሰጡ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና በክልሉ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በራፎች ላይም ተገኝተው ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ደረጃ በብዙዎቹ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማሩ ሒደት ተጀምሮ በሚገኝበት በአሁኑ ጊዜ፣ የተፈናቃይ ቤተሰብ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ባለመቻላቸው፣ “የእነርሱም መብት ይከበር፤” ብለዋል ሰልፈኞቹ፡፡

የተፈናቃዮቹን ሰልፍ ከአስተባበሩት አንዱ አቶ ካልኣዩ ገብረ እግዚአብሔር፣ የሰልፉ ዓላማ፥ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱና ሥርጭቱ ተቋርጦ የሚገኘው ሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀጥል ለመጠየቅ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት፥ ለተፈናቃዮቹ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ለመጠየቅ የተካሔደ መኾኑን አስተባባሪው አብራርተዋል።

የተፈናቃይ ሰልፈኞቹ ተወካዮች፣ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ዐማኑኤል አሰፋ ጋራ የተወያዩ ሲኾን፣ ጥያቄያቸውን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንደሚቀበለውና እንደሚሠራበትም የጽሕፈት ቤት ሓላፊው አረጋግጠውላቸዋል፡፡

በሰብአዊ ርዳታ ላይ ተፈጽሟል የተባለውን ምዝበራ የማጣራቱ ሒደት መቀጠል እንዳለበት የገለጹት አቶ ዐማኑኤል፣ ከዚኽም ጋራ፣ ለጋሽ ተቋማት በጊዜያዊነት ያቋረጡትን የርዳታ ሥርጭት እንዲቀጥሉ መደረግ እንዳለበት፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አቋም እንደኾነ አመልክተዋል፡፡

በመቐለ ከተማ ዛሬ በተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ተሳትፈዋል፡፡

XS
SM
MD
LG