በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለስልታዊ እና ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ኢሰመኮ ጠየቀ


ለስልታዊ እና ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ኢሰመኮ ጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:47 0:00

ለስልታዊ እና ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ኢሰመኮ ጠየቀ

በኢትዮጵያ የሚፈጸመው ስልታዊ እና ተደጋጋሚ የዘፈቀደ እስራት፣ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

ኢሰመኮ፣ ከሚያዝያ 2010 እስከ ሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ባሉት አምስት ዓመታት “ነጻነታቸውን ተነፍገዋል፤” ባላቸው ሰዎች መብቶች ጉዳይ ባለ130 ገጽ የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡን የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ አገራዊ ዐውዶች እና ኹነቶች ውስጥ የተራዘመና የዘፈቀደ እስራት እንዲሁም በታሳሪዎችና በቤተሰቦቻቸው ላይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በስፋት እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ አንጻራዊ መረጋጋት በሚኖርበት ጊዜ፣ በእስረኞች አያያዝና በማቆያ ስፍራዎች ላይ የተወሰኑ መሻሻሎች እንደታዩ የገለጹት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ፣ በግጭት ወቅት ግን ይፈጸማሉ ያሏቸውን የመብቶች ጥሰቶች ለማስቆም ጠቃሚ ነው ያሉትን ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

በመደበኛነት ከሚደረጉ የሰብአዊ መብቶች ምርመራዎች በተጨማሪ፣ ብሔራዊ ምርመራ ማድረግ አንዱ የምርመራ ሥነ ዘዴ እንደኾነ ኮሚሽኑ ጠቁሟል። ይኸውም፣ በስፋት እና በተደጋጋሚ ውስብስብ በኾነ መልኩ በሚፈጸሙ፣ ብዙዎችን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሰለባ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል፡፡

ብሔራዊ ምርመራ በልዩ ልዩ ሀገራት የተለመደ መኾኑን የገለጹት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ በኢትዮጵያ ምርመራው ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ምርመራውን በመላው ኢትዮጵያ የማካሔድ ዕቅድ ቢኖረውም፣ ከአገሪቱ ስፋት አንጻር ፈታኝ በመኾኑ፣ ሀገራዊ ምስሉን ሊያሳዩ ይችላሉ ተብሎ በታመነባቸው፣ ሰፊ ሕዝብ እና የቆዳ ስፋት ባላቸው፣ እንዲሁም ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸውን ክልሎች መርጦ ምርመራ ማከናወኑን ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም የሶማሊያ ክልሎች፣ ኮሚሽኑ ምርመራውን ያካሔደባቸው እንደኾኑ የዘረዘሩት ወይዘሮ ራኬብ፣ ምርመራ ማድረግ ያስፈለገበትንና መቼቱ የተመረጠበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትንና መንሥኤዎቻቸውን ከማስቆም ባለፈ፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለባቸውም፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ አሳስበዋል፡፡

ኢሰመኮን ጨምሮ የተለያዩ አገራዊ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች፣ በግጭት እና በሌሎችም ዐውዶች ውስጥ በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመ እንደኾነ በሪፖርቶቻቸው ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ግለሰቦች እና ቡድኖችም መሰል አቤቱታዎችን በልዩ ልዩ መንገዶች እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም፣ የሕዝብ ተወካዮችን ጨምሮ በአስቸኳይ ዐዋጁ የታሰሩ 14 ሰዎች “አካላዊ፣ ሞራላዊ እና ሥነ ልቡናዊ ጥቃት እየተፈጸመብን ነው፤” ሲሉ፣ ባለፈው ሳምንት በደብዳቤ አቤቱታ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኢሰመኮ ባወጣው የብሔራዊ ምርመራ ሪፖርት ላይ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስተያየት እና ምላሽ ለማግኘት፣ በመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ የእጅ ስልክ ላይ ደውለንና በጹሑፍም ጠይቀን ምላሽ አላገኘንም።

ኾኖም፣ በመንግሥታዊ መዋቅር ሥር ይፈጸማሉ ተብለው ከዚኽ ቀደም የሚቀርቡትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሪፖርቶች፣ መንግሥት በአብዛኛው ውድቅ ማድረጉ፣ የተወሰኑትንም እንደሚያጣራና ርምጃ እንደሚወስድ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG