በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ አካላት ሲቪሎች እንደሚገደሉ ኢሰመኮ አስታውቀ


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት “በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከሕግ ወይም ፍርድ ውጭ በመፈጸም ላይ ያለ ግድያ እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲል ትናንት ዓርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች በሰበሰበው መረጃ መሠረት፣ በርካታ ሲቪል ሰዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው ለመረዳት ተችሏል ብሏል።

“በተኩስ ልውውጦች ወይም በከባድ መሣሪያ ተኩስ ከሚሞቱ ሰዎች መካከል በመንገድና በእርሻ ሥራ ላይ እንዲሁም በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ሰዎች ጭምር የሚገኙ መሆኑን ቤተሰቦች እና የዐይን ምስክሮች ያስረዳሉ” ብሏል የኮሚሽኑ መግለጫ።

ኮሚሽኑ ባሰባሰባቸው መረጃዎች መሠረት የትጥቅ ግጭቱ ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎች መስፋፋቱን፣ በነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ተባብሶ መቀጠሉን ያመለክታሉ ብሏል።

“በግጭቱ ዐውድ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከሕግ/ፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል።

“ከሕግ/ፍርድ ውጪ የሆኑ ግድያዎች ሰለባ ከሆኑ ሰዎች መካከል ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ ሰዎች፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ ‘የጦር መሣሪያ ደብቃችኋል አምጡ’ በሚል የተያዙ ሰዎች፣ የሰዓት እላፊ ገደቦችን ተላልፈው የተገኙ ሲቪል ሰዎችና በቁጥጥር ስር የዋሉ የታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) አባላት የሚገኙበት ሲሆን፤ በኮሚሽኑ እና በአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርዱ አማካኝነት የተሟላ ምርመራ ሊደረግበት የሚያስፈልግ ነው” ሲል መግለጫው አክሏል።

በተለይ በአማራ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ ዐውዱ የተስፋፋና የዘፈቀደ እስር እንደተፈጸመ አመልክቷል።

በሲቨል ሰዎች ላይ ግድያ በፈጸሙና በዘፈቀደ እስራት ላይ በተሳተፉ አካላት ላይ አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ኮሚሽኑ ጥሪ አድርጓል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG