በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደመቀ መኮንን “ተተኩ”


አቶ ደመቀ መኰንን
አቶ ደመቀ መኰንን

የኢትዮጵያው ገዥ ብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንቱን አቶ ደመቀ መኮንንን “በክብር” ማሰናበቱን ዛሬ አስታወቀ።

ፓርቲው መልዕክቱን ያወጣው ላለፉት አምስት ቀናት አዲስ አበባ ውስጥ ያካሄደውን የሥራ አስፈፃሚና የማዕከላዊ ኮሚቴዎች ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ነው።

ከፓርቲው መሥራቾች አንዱ የሆኑትንና ላለፉት አምስት ዓመታት በፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉትን አቶ ደመቀን ከኃላፊነታቸው የሸኘው በፓርቲው የአመራር መተካካት መርኅ መሠረት መሆኑን ገልጿል።

በምትካቸው የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ተመስገን ጥሩነህ መመረጣቸውንም ብልፅግና ፓርቲ አስታውቋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በካቢኔው ውስጥ ይዘዋቸው ስለቆዩት የመንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነቶች እስካሁን ከመንግሥቱ የወጣ መረጃ የለም።

አቶ ደመቀ መኮንን የፖለቲካ ጉዟቸውን የጀመሩት በ1980ዎቹ የቀደሙ ዓመታት በብሔረ-አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አባልነት ሲሆን የአማራ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ፣ በ1997 ዓ.ም. ደግሞ የክልላዊ መንግሥቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል።

አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀ መንበርና ከኅዳር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀ መንበር ሆነዋል። ለፌደራሉ ፓርላማ እንደራሴነት ተመርጠው ያገለገሉ ሲሆን በትምህርት ሚኒስትርነትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሠርተዋል።

በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የተዋቀረው ብልፅግና ፓርቲ የመንግሥት ሥልጣን ሲቆናጠጥ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የሆኑት አቶ ደመቀ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

በ1980 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ ያገኙት አቶ ደመቀ መኮንን በግጭት አፈታት ላይ ጥናት አድርገው ከእንግሊዙ ብራድፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ (ማስተርስ) ዲግሪያቸውን ይዘዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG