በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤርትራዊያን ስደተኞች እየታሰሩ ነው - ኢሰመኮ


ኤርትራዊያን ስደተኞች እየታሰሩ ነው - ኢሰመኮ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:19 0:00

ኤርትራዊያን ስደተኞች እየታሰሩ ነው - ኢሰመኮ

ኢትዮጵያ ውስጥ “ኤርትራዊያን ስደተኞችና ከለላ ጠያቂዎች በዘፈቀደ እየታሠሩ ነው” ሲል የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።

ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡ ስደተኞችም ፖሊስ ያለ ምክንያት እያየዘ እንደሚያሥራቸውና መብቶቻቸው እየተጣሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በጉዳዩ ላይ በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጥ ገልፆልናል።

ኤርትራዊያን ስደተኞችና ከለላ ጠያቂዎች በዘፈቀደ እየታሠሩ ነው”

‘ለደኅንነቴ እሠጋለሁ’ በሚል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ ኤርትራዊ ስደተኛ፣ “መታወቂያችሁ አልታደሰም” ተብለው ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ይዝናኑ ከነበረበት በፖሊስ መወሰዳቸውንና እርሱ አንድ ሣምንት ታስሮ መለቀቁን ይናገራል። ጣቢያው ውስጥ አብዛኞቹ ኤርትራዊያን የሆኑ ወደ ስድሣ እሥረኞች እንደነበሩ ገልጿል።

በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የስደተኞች፣ የፍልሰተኞችና የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ክፍል ዳይሬክተር፤ እንጉዳይ መስቀሌ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የታሰሩ ኤርትራዊያን መኖራቸውን እንደሚያውቁ ገልፀዋል።

“ህዩመን ራይትስ ፈርስት” የሚባል ኢትዮጵያዊ የመብቶች ተሟጋች ድርጅትም ስደተኞቹ እየተያዙ ያሉት ያለምክንያት እንደሆነና ከኅዳር ጀምሮ ጥቆማዎች እየደረሱት መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ መብርሂ ብርሀነ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ያናገርነው ስደተኛ ታስሮ ስለነበረበት ቦታ፣ ስለተለቀቀበት ሁኔታና አብረውት ስለነበሩ ሌሎችም ኤርትራዊያን ለቪኦኤ በዝርዝር ተናግሯል።

እሥር ቤት ውስጥ የነበረው አያያዝ ጥሩ እንዳልሆነ፣ ንፅህና እንደሌለው፣ ምግብና ውኃም በአግባቡ እንደማይቀርብ፣ እሥረኞች እንደሚደበደቡ አውስቷል፡፡ እርሱም የተለቀቀው ገንዘብ ከፍሎ እንደሆነ ገልጿል። ሰነድ የሌላቸው ሃያ የሚሆኑ እሥረኞችን ግን ወደ ሌላ እስር ቤት እንደወሰዷቸው አመልክቷል፡፡

ሌላ ከቪኦኤ ጋር የተነጋገረ ስደተኛም የታሰሩ ስደተኞችን እየተዘዋወረ እንደሚጠይቅ ገልፆ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ፖሊስ ጣቢያ 24፣ ሳሪስ አዲሱ ሰፈር ፖሊስ ጣቢያ 27 ስደተኞች እንዳሉ እንደሚያውቅ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኗ እንጉዳይ መስቀሌም ተመሣሣይ ጥቆማዎችና ስሞታዎች እንደሚደርሷቸው ተናግረዋል።

የታሠሩት ስደተኞች የታደሰ መታወቂያ ያላቸውና መታወቂያቸው ያልታደሰ፣ ሰነድ የሌላቸውም እንደሆኑ ዳይሬክተሯ ጠቁመው ኮሚሽናቸው ከኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ጋር መነጋገሩን ገልፀዋል። አገልግሎቱ ሰነድ ያላቸውን ከፖሊስ ጋር ተነጋግሮ እንደሚያስፈታ ቃል እንደተገባላቸው፤ ሰነድ ስለሌላቸው ከለላ ጠያቂዎች ጉዳይ ግን “አይመለከተኝም” ማለቱን አመልክተዋል። ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋርም መገናኘታቸውን ተናግረዋል።

ከለላ ጠያቂዎችን በግድ ወደመጡበት መመለስ መብትን መርገጥ መሆኑን የገለፁት እንጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለምአቀፍ ስምምነቶችን እንዲያከብር፣ የስደተኞችና የከለላ ጠያቂዎችን ምዝገባ እንዲጀምር አሳስበዋል።

የአሜሪካ ድምፅ በስልክ ያነጋገራቸው የስደተኞችና የተመላሾች አገልግሎት የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ በአካል ንጉሤ በኮሚሽኑ የተነሱትን አስተያየቶችና ቅሬታዎች እንደሚያውቁ ገልፀው “በቅርቡ የተጠናቀረ ምላሽ ይሰጥባቸዋል” ብለዋል። ከፌደራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስም ምላሽና አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG