ዋሽንግተን ዲሲ —
ቻይና፣ በደቡብ ቻይና ባህር ይገቡኛል ከምትላቸው ደሴቶች አንዱ ላይ የተራቀቀ ተምዘግዛጊ ሚሳኤል መሳርያ ተክላለች። ይህ እርምጃ በቻይናና በጎረቤት ሃገሮች መካከል ያለውን ውጥረት ያባብሳል ተብሎ ይታመናል።
የታይዋን መከላከይ ሚኒስቴር የሚሳኤል ባትሪዎቹ የፓርሰል ደሴት ሰንሰለት አካል በሆነው ዉዲ ደሴት ላይ ተተክለዋል ሲል ዛሬ ገልጿል።
ፎክስ ኒውስ (Fox News) የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ ቴሌቪዥን ጣብያ ባለፈው እሁድ ያሳየው ምስል የስምንት ተምዘግዛጊ ሚሳይል አምጣቂዎች ሁለት ባትሪዎችንና ራዳርን ያሳያል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው የሚሳይል ተከላው ወሬ የምዕራቡ አለም ሚድይ ፈጠራ እንጂ ቻይና በደቡብ ቻይና ባህር ላይ ያላት እንቅስቃሴ እውነታን አያንጸባርቅም ብለዋል።