ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና ወደ ከባቢ አየር የሚለቅቋቸውን በካይና ሙቀት አማቂ ጋዞችን መጠን ለመቀነስ ያስችላል የተባለ አዲስ ዕቅድ ይፋ አደረጉ፡፡
ካርቦንዳይኦክሳይድን የመሳሰሉ የተፈጥሮ አካባቢን በካይ ጋዞችን ወደ አየር በመልቀቅ በዓለም መሪ የሆኑት ሁለቱ ሃገሮች የደረሱበት ስምምነት ጎጂ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ግዙፍ አስተዋፅዖ ያደርጋል ተብሏል፡፡
ዕቅዱ በሁለቱ ሃገሮች መካከል በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄደ ያለው ስብሰባ የላቀ ውጤት መሆኑ ተነግሯል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ እአአ በ2025 ዓ.ም (በመጭዎቹ አሥር ዓመታት ማለት ነው) የተቃጠሉ በካይ ጋዞች ልቀት መጠን ከ26 እስከ 28 ከመቶ ለመቀነስ መስማማቷን ቤጂንግ ላይ በተካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የምጣኔ ኃብት ትብብር ስብሰባ ላይ የተገኙትና በቻይና ይፋ ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አስታውቀዋል፡፡
የቻይና ፕሬዚዳንት ቺ ዪፒንግም በመጭዎቹ 15 ዓመታት (እአአ እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ) የሃገሪቱ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀት መጠን ከ26 እስከ 28 ከመቶ እንደሚቀንስ ተናግረዋል፡፡
በ2030 ዓ.ም ቻይና የፀሐይና የነፋስን ከመሳሰሉ ታዳሽና ንፁህ ምንጮች የምታመርተውና የምትጠቀመው ኢነርጂ ወይም ኃይል መጠን ከአጠቃላዩ 20 ከመቶ እንደሚደርስ ቻይናዊው ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል፡፡
ትልቋ የአካባቢ በካይ ቻይና እንዲህ ዓይነት ቀን ቆርጣ ግዴታ ውስጥ ስትገባ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ይህ የሁለቱ የዓለም ግዙፍ ምጣኔሃብቶች መሪዎች ስምምነት ለዓለምአቀፉ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ንግግሮች ወደፊት መግፋት ጉልበት ይሰጣል ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ባወጡት ፅሁፍ አመልክተዋል፡፡
ስምምነቱ ለአሜሪካና ለቻይና ግንኙነቶች ዋና የሚባል የማዕዘን ድንጋይ ነው ሲሉ ቤጂንግ ላይ በተዘጋጀ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የቻይናው አቻቸው በሁለቱ ሃገሮች መካከል ውጥረት ይፈጥሩ በነበሩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ያላቸውን ዝግጁነት አድንቀዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ሚያንማር ውስጥ ለሚካሄደው አሴአን በሚል ምኅፃር በሚጠራው የደቡብ ምሥራቅ እስያ ሃገሮች ሕብረት ስብሰባ ላይ ለመገኘት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ዋና ከተማይቱ ናይፒዳው ገብተዋል፡፡
ሚያንማር በፖለቲካና በምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ ዕድገት ብታስመዘግብም በአንዳንድ ጉዳዮች ወደኋላ ቀርታለች ማለታቸውን ኢራዋዲ የሚባል የሃገሩ መፅሔት በዛሬ ዕትሙ አውጥቷል፡፡
ሚስተር ኦባማ አድርገውታል በተባለው በዚህ ቃለምልልስ ላይ ሃገሪቱ የኋልዮሽ ተጉዛበታለች ያሏቸውን ነጥቦች መፅሔት ባያወጣም ከሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ጤይን ሴይን እና ከተቃውሞው መሪ አን ሳን ሱክዪ ጋር በሚያደርጓቸው ውይይቶች ያነሷቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡