በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደሳለኝ ጫኔ ታሰሩ


ደሳለኝ ጫኔ ታሰሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:23 0:00

ደሳለኝ ጫኔ ታሰሩ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ፓርቲን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ትላንት፣ ረቡዕ፣ ጥር 22 / 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ በፖሊስ ተወስደው መታሰራቸውን አንድ የቤተሰባቸው አባል ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስና መለዮ ያጠለቁ ሁለት ሰዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የታጠቁ ሁለት ሲቪል ለባሾች “በሕግ ይፈለጋሉ” ብለው ከመኖሪያ ቤታቸው እንደወሰዷቸው፤ “ለደኅንነቴ እሠጋለሁ” በሚል ማንነታቸውን እንዳንገልፅ የጠየቁን አንድ የዶ/ር ደሳለኝ ቤተሰብ አባል ገልፀዋል።

የፖሊስ ባልደረቦቹና የፀጥታ ሠራተኞቹ ዛሬ ኀሙስ፤ ጠዋት ዶ/ር ደሳለኝን ይዘው መመለሳቸውንና ቤታቸውን ፈትሸው ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስና ሰነዶችን፣ እንዲሁም እራሣቸውን አቶ ደሳለኝንም ይዘው መሄዳቸውን እኒሁ ዘመድ አመልክተዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማረፊያ ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል። የዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ጠበቃ አቶ ሰሎሞን ገዛኸኝ ጠበቆች ደንበኛቸውን ማግኘት የሚችሉት ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ መሆኑን ጠቅሰው ነገ፤ ዓርብ ደንበኛቸው ታስረው ወደሚገኙበት እንደሚሄዱ ገልፀዋል።

ከዚህ በፊት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሠሩ ሌሎች ደንበኞቻቸውን ማግኘት እንዳልተፈቀደላቸው አቶ ሰሎሞን አስታውሰው ዶ/ር ደሳለኝ የተያዙት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውጭ በሆነ ምክንያት ከሆነ ሊያገኟቸው እንደሚችሉ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባል ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ትናንት ረቡዕ ምሽት ከመኖሪያ ቤታቸው ተይዘው መታሰራቸውን አንድ የቤተሰባቸው አባል ገለፁ።

መረጃ የጠየቅነው ፌደራል ፖሊስ፣ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር የሚያዙ ሰዎችን መረጃ የሚሰጠው ኮማንድ ፖስቱ ብቻ ነው” ብሏል።

ከአብን መሥራቾች አንዱና የንቅናቄው የመጀመሪያ ሊቀ መንበር የነበሩት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወዲህ የተያዙ ሁለተኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የአብንም አባል ናቸው።

ሌላው የአብን አመራር አባልና እንደራሴ አቶ ክርስትያን ታደለ አማራ ክልል ውስጥ ባለው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት “በክልሉ ውስጥና እንደ አስፈላጊነቱ በመላ ኢትዮጵያም ተግባራዊ ይደረጋል” የተባለውና የኃይል ጊዜው ሰሞኑን የሚያበቃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በተደነገገበት ዕለት፣ ሐምሌ 28 / 2015 ዓ.ም. ተይዘው ታስረዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሣ ተሻገርና የሰላም ሚኒስትር ደ’ኤታ የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ጨፌ አባል አቶ ታየ ደንደአም እሥር ቤት ያሉ እንደራሴዎች ናቸው።

የዶ/ር ደሳለኝን መታሠር አስመልክቶ እስከ አሁን ከፖሊስም ሆነ ከሌላ የመንግሥት አካል የወጣ መረጃ የለም።

ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተገናኘ የሚያዙ ሰዎችን በሚመለከት መረጃ የመስጠት ሥልጣን የኮማንድ ፖስቱ እንደሆነ” ነግረውናል።

በፓርላማው ውስጥና በውጭም ገዢውን ፓርቲ በመሞገት የሚታወቁት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ባለፈው ሰኔ 29 በተካሄደው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ሥልጣናቸውን እንዲለቅቁና ምክር ቤቱም እንዲበተን” ጠይቀው ነበር።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG