በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአዋጁ መቀጠል ላይ የሚጋጩ ሃሣቦች አሉ


በአዋጁ መቀጠል ላይ የሚጋጩ ሃሣቦች አሉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:49 0:00

በአዋጁ መቀጠል ላይ የሚጋጩ ሃሣቦች አሉ

በአማራ ክልል ላይ ተጥሎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ለአራት ተጨማሪ ወራት እንዲራዘም ፓርላማው ዛሬ ወስኗል።

ላለፉት ስድስት ወራት ተፈፃሚ ሆኖ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲራዘም ለምክር ቤቱ ጥያቄ ያቀረቡት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌድዮን ቲሞጢዎስ የአዋጁን ጊዜ ማራዘም ያስፈለገው ከአማራ ክልል በተጨማሪ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ያሉ “አንዳንድ አዝማሚያዎችና የፀጥታ ሥጋቶችንም ታሳቢ በማድረግ” መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም “በዕቅድ የተያዙ” ያሏቸውን “ቀሪ ሥራዎችንም ለመሥራት” እና “የአስቸኳይ ጊዜ መምሪያ ጠቅላይ ዕዙ አዋጁ ቢራዘም ለህዝብ ደኅንነትና ሠላም በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን በመደምደሙ” እንደሆነ አክለው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ግን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው መራዘሙ እንዳሳዘናቸው አስተያየቶቻቸውን ለአሜሪካ ድምፅ የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

አዋጁ በክልሉ “አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን እንደረዳ” መንግሥት ተናግሯል።

ለደኅንነቴ እሰጋለሁ በሚል ማንነታቸውን እንዳናሳውቅ የጠየቁ አንዲት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመንቀሳቀስ ነፃነትን በከፍተኛ ሁኔታ ገድቧል፤ በፀጥታ ኃይሎች ጥቃት የሚፈፀምባቸው ወጣቶች ቁጥር ከመጨመሩ ውጭ ያመጣው ለውጥ የለም” ብለዋል።

ሌላ የከተማው ነዋሪ ደግሞ “ከባሕር ዳር ከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ሰላም አለ ማለት እንደማይቻል” ጠቁመው በዚህም ሳቢያ ወደ ከተማዪቱ በቂ የምግብ አቅርቦት እንደማይገባ፣ የኑሮ ውድነቱ ነዋሪውን እየተፈታተነው መሆኑን” ተናግሯል።

“አዋጁ የተጨበጠ ሠላምና መረጋጋት አላመጣም” ሲሉ ከጎንደርና ከሰሜን ሸዋም አስተያየታቸውን ለቪኦኤ የሰጡ ነዋሪዎች “በመንግሥት ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ያለው ውጊያ በድርድር እንዲፈታ” መክረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው መራዘም እንደሚያሳስበው ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

በግጭቶች ውስጥ የሚደርሱ ጉዳቶች፣ ሰብአዊ ቀውሶችና ከፍርድ ውጭ የሚፈፀሙ የተራዘሙ እሥራቶች ከአሳሳቢ የመብቶች ጥሰቶች ውስጥ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነር ዳንኤል መፍትኄው ውይይት እንደሆነ መክረው “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና መንግሥት የአዋጁን አስፈላጊነት፣ ህጋዊነትና ተመጣጣኝነት በሚገባ እንዲያጤኑ” ከፓርላማው ውሣኔ በፊት አሳስበው ነበር።

የዋና ኮሚሽነሩን መልዕክትና ሃሣብ ያጠናከሩት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ራኬብ መሰለ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል “የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው እንዲቀጥል መደረጉ “ትክክል ነው ብለው እንደማያምኑ” ተናግረዋል። “ችግሮችን በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መፍታት የተሻለ አማራጭ ነው” የሚሉት ወ/ሮ ራኬብ ግጭቶችም በውይይት መፈታት እንዳለባቸው በድጋሚ አሳስበዋል።

ፓርላማው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለመነጋገር ከመሰብሰቡ በፊት የመብቶች ኮሚሽኑ ልኮት በነበረ ምክር አዘል ሃሣብ ላይ “አዋጁ እንዳይፀድቅ፣ የሚፀድቅ ከሆነም ዕድሜው ከአንድ ወር ወይም ከጥቂት ሣምንታት እንዳይበልጥ” ጠይቆ ነበር።

በፓርላማው የዛሬ፤ ጥር 24 / 2016 ዓ.ም. ውሎ ላይ ከመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በስተቀር እንዲገኝ የተፈቀደለት ሌላ ሚድያ አልነበረም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG