በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሸዋ ሮቢት ላይ ዓርብና ቅዳሜ ግጭት ነበር - ነዋሪዎች


ሸዋ ሮቢት ላይ ዓርብና ቅዳሜ ግጭት ነበር - ነዋሪዎች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:05 0:00

ሸዋ ሮቢት ላይ ዓርብና ቅዳሜ ግጭት ነበር - ነዋሪዎች

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማ አካባቢ ባለፈው ሣምንት መጨረሻ በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ሲቪሎች መገደላቸውን የዐይን እማኝ ነን ያሉ ተናግረዋል።

“በመከላከያ ወታደሮችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ዓርብና ቅዳሜ ተካሄደ ያሉት የተኩስ ልውውጥ ከባድ መሣሪያም የተቀላቀለበት ነበር” ብለዋል እማኞቹ።

ከተማዪቱ አሁን የተረጋጋች ቢሆንም ስለግጭቱና ‘ተጎድተዋል’ ስለተባሉ ሰዎች ከባለሥልጣናቱ ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

በተኩሱ ውስጥ የተገደሉና የቆሰሉ ሰዎችን ማየታቸውን የቪኦኤ ዘጋቢ ባለፈው ቅዳሜ በስልክ ያገኛቸው ሸዋ ሮቢት ውስጥ እንደሚኖሩ የገለፁ አንድ የአፋር ተወላጅ ተናግረዋል።

የወንድማማች ፀብ ሲሉ ላወገዙት ውጊያ በተለይ መንግሥት ዘላቂ መፍትኄ እንዲያበጅለት ጠይቀዋል።

በተመሣሳይ ሁኔታ ከደኅንነታቸው ጋር በተያያዘ ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁና ድምፃቸውንም ማሰማት ያልፈለጉ አንድ የሸዋሮቢት ጤና ጣቢያ ባልደረባ በተኩስ ልውውጡ ጉዳት ደርሶበት ከነበረና ታክሞ ከተመለሰ አንድ ሰው ሌላ ለህክምና የሄደ ሰው እንዳልነበረ ገልፀዋል።

ፀጋ ታደሰ የተባሉ እናት የ11 ዓመት ሴት ልጃቸው በተኩስ ልውውጡ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሳለች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት ህክምና ማግኘቷንና አሁን እያገገመች መሆኗን ተናግረዋል።

የአፋር ተወላጅ መሆናቸውን ገልፀው የነበሩት ነዋሪ በተለይ ከሸዋ ሮቢት ቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ራሳ አካባቢ ግጭት በተደጋጋሚ እንደሚስተዋል ጠቁመዋል።

ከሰሜን ሸዋ ዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊና ከሸዋ ሮቢት ከንቲባ ስላለው ሁኔታ ማብራሪያ ለማገኘት የተደረጉ ጥረቶች አልተሳኩም።

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የአማራ ክልል የአምስት ወራት ሥራ አፈፃፀም ግምገማን መሠረት አድርጎ ባወጣው ዘገባ “ክልሉ ውስጥ ሰላም እየሰፈነ በመሆኑ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ጨምሮ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የልማት ሥራዎች በተሟላ ሁኔታ መከናወን ጀምረዋል” መባሉን ጠቅሷል።

በሸዋ ሮቢቱ የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ከደሴ ወደ አዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ የነበሩ የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎቶች ተቋርጠው እንደነበር ታውቋል።

አሁን ከተማዪቱ መረጋጋቷና ባንክና ግብይትን ጨምሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መቀጠላቸው ቢገለፅም አንዳንድ ነዋሪዎቿ አሁንም ሥጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG