በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ተኩስ ሳይቆም ዜጎችን ለማውጣት እንደሚያዳግተው ገለጸ


በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ተኩስ ሳይቆም ዜጎችን ለማውጣት እንደሚያዳግተው ገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:54 0:00

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ ተኩስ ሳይቆም ዜጎችን ለማውጣት እንደሚያዳግተው ገለጸ

በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መገኛው መሀል ኻርቱም ነው፡፡ መዲናዪቱ ኻርቱም ደግሞ፣ በአሁኑ ወቅት፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል ዋና የፍልሚያ ዐውድማ ኾናለች፡፡ ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ፣ ሁለቱም ኃይሎች፣ ለሁለተኛ ጊዜ ተኩስ ለማቆም ቢስማሙም በቃላቸው አልተገኙም፡፡

በሌላ በኩል ሀገራት፣ ዋና ከተማዪቱ ኻርቱም፣ ሥርዐተ አልቦነት የሰፈነባት አደገኛ ስፍራ ኾናለች፤ በሚል፣ ዜጎቻቸው፣ በጎዳናዎቿ ከመዘዋወር እንዲታቀቡ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡ በመሀል ከተማዋ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም የጥቃት ሰለባ ከመኾን አለመዳኑ ተዘግቧል፡፡

ታዲያ፣ ይህ ኹሉ እየኾነባት ወዳለችው መሀል ኻርቱም አምርቶ፣ ወደ ኤምባሲው ለመዝለቅ የሚነሣሣ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይኖራልን? በዚኽ አስቸጋሪ ቦታ እና ኹኔታ የሚገኘው ኤምባሲው እና ሠራተኞቹስ፣ ምን ዐይነት አገልግሎት ለመስጠት ይችላሉ? ለእነዚኽ እና ተያያዥ ጥያቄዎቻችን፣ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

“ከኤምባሲው ለመውጣት እና ለመግባት አስቸጋሪ ነው፤” የሚሉት አምባሳደር ይበልጣል፣ ለዲፕሎማቶችም ሳይቀር ወደ ውጭ ለመውጣት አስጊ በመኾኑ፣ ሁሉም በያለበት የሚኾነውን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ኤምባሲው፣ በተባራሪ ጥይቶች ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ያስታወቁት አምባሳደር ይበልጣል፣ የተጎዳ ሰው ግን አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በካርቱም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፥ የጉዳቱ ሰለባ የኾኑ እንዳሉ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል፡፡ በተባራሪ ጥይት የተገደሉም የቆሰሉም መኖራቸውን ጠቅሰው፣ በቁጥር ምን ያህል እንደኾኑ ኤምባሲው ለማረጋገጥ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ “አንዳንዶች ዐሥር ናቸው ይሉናል፤ ሌሎችም አምስት ናቸው ይሉናል፤” ያሉት አምባሳደር ይበልጣል፣ ቁጥሩ ከተነገረው ሊበልጥም ሊያንስም እንደሚችል ያመላክታሉ፡፡

ዋናው ችግር፣ በከተማው ከሚሰማው የተኩስ ልውውጥ የተነሣ፣ መንገዱ ለአደጋ በእጅጉ ተጋላጭነት ያለው በመኾኑ፣ ለኤምባሲው ሪፖርት ለማድረስ እና የተሟላ መረጃ ለማግኘት አዳጋች እንዳደረገው አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሱዳን የኢትዮጵያውያን ዜጎችን ኹኔታ በቅርበት እየተከታተለ መኾኑን በዛሬው ዕለት ቢገልጽም፣ ዜጎችን ለማውጣት የተኩስ አቁም ስምምነት መኖር እንዳለበት፣ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ያስገነዝባሉ፡፡

በአገሪቱ ከገባችበት አስከፊ ጸጥታዊ ኹኔታ አኳያ፣ ሰዎችን ከአስቸጋሪ ሥፍራዎች በማስወጣት ሒደት፣ “ምንም ዐይነት ጥቃት እንደማይደርስባቸው ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤” ሲሉ፣ አምባሳደሩ አክለው አሳስበዋል።

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ ጋራ የተደረገውን ቃለ ምልልስ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

XS
SM
MD
LG