በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልዕለ ጀግና (ሱፐር ሂሮ)


 የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልዕለ ጀግና (ሱፐር ሂሮ)
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:56 0:00

የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልዕለ ጀግና ገፀባህሪ የሆነው ጀምበር በ11 የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ሊሰራጭ ነው። በኢትዮጵያ ባህል፣ ታሪኮች እና አፈ ታሪኮች ላይ ተመስርቶ የተፃፈው ይህ መፅሃፍ አፍሪካዊ ህፃናትን ከማንነታቸው ጋር የሚያቆራኝ፣ በራስ መተማመንን የሚያጎለብት እና ስኬትን የሚያስተምር መፅሃፍ ሲሆን፣ ደራሲው ብስራት ደበበ የመሰረተው ኢታን ኮሚክ ተቋም፣ በሌሎች አፍሪካዊ ፀሃፊያን የተደረሱ አፍሪካዊ ሰን-ስዕል መፅሃፍትንም ያሳትማል።

እ.አ.አ በ2018 ሆሊውድ ለተመልካች ያቀረበው 'ብላክ ፓንተር' ፊልም - ባልተለመደ መልኩ - አፍሪካውያንን ባለስኬት ጀግኖች አድርጎ በመሳል፣ በተለይ አፍሪካዊያንና ጥቁሮችን ክብር ያጎናፀፈ ፊልም ነበር። የቀድሞ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ጥቁሮች ለብላክ ፓንተር አድናቆታቸውን እየቸሩ ባሉበት ወቅት ታዲያ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ልዕለ ጀግና (ሱፐር ሂሮ) በሰን-ስዕል (ኮሚክ ቡክ) አማካኝነት ለገበያ በቅቶ ነበር።

'ጀንበር' የሚል ስያሜ የተሰጠውን ልዕለ ሀያል ወይም ሱፐር ሂሮ የፈጠረው ብስራት ደበበ የ13 አመት ለጋ ወጣት እያለ ወደ አሜሪካ ሲመጣ ይከታተላቸው የነበሩት እና በዓለም ዙሪያ በስፋት የሚታወቁት እንደ 'ሱፐር ማን' እና 'ባት ማን' የመሳሰሉት የሆሊውድ ገፀባህሪያት ሲመለከት 'ለምን ጥቁር አልሆኑም፣ ለምን እኔን የመሰሉ ኢትዮጵያዊ ማንነት ያላቸው ልዕለ-ጀግናዎችስ የሉም 'የሚል ጥያቄዎች እንደፈጠሩበት ያስታውሳል።

እ.አ.አ በ1966 ዓ.ም በአሜሪካ ሰን-ስዕል መፅሃፎች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ጥቁር ልዕለ ሀያል (ሱፐር ሂሮ) ገፀባህሪ ማርቭል በተሰኘው አሳታሚ የታተመው ብላክ ፓንተር ቢሆንም ከዛ በፊትም የተፃፉ እንደ 'ላየን ማን' የተሰኙ ጥቁር ጀግና ገፀባህሪያትም እንደነበሩ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ።

እነዚህ ጥቁር ልዕለ-ጀግናዎችን የያዙ መፅሃፍት በዋናነት ጥቁር ህፃናት ራሳቸውን የሚመስሉ ገፀባህሪያትን እንዲያዩ እና እንዲነቃቁ የሚያደርጉ ሲሆን በማህበረሰባቸው ውስጥ ከፍ ያለ ስራን እንዲሰሩ ያነሳሳቸዋል። ብስራትም ጀምበር የተሰኘውን የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ልዕለ ጀግና ሲፈጥር ይህን አስቦ እንደሆን ይናገራል።

ከ56 ዓመታት በፊት በስቲቭ ዲትኮ እና ስታን ሊ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፃፈው ስፓይደር ማን የተሰኘው ልዕለ ጀግና ገፀባህሪ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ዛሬም ድረስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ህፃናት ገፀባህሪውን መምሰል ይመኛሉ። ብስራት እንደሚለው የዚህ ምክንያቱ ሱፐር ማን ከማደሰት በተጨማሪ ማንነትን የመቅረጽ አቅም ስላለው ነው።

ብስራት ከአምስት አመት በፊት ያቋቋመው ኢታን ኮሚክስ የተሰኘው ተቋም ከጀምበር በተጨማሪ ዙፋን እና ሃዊ የተሰኙ ልዕለ-ሀያል ገፀባህሪያትንም ከሌሎች የአፍሪካ ፀሃፍት ጋር በመሆን አሳትሞ ለገበያ አቅርቧል። በተለይ ዙፋን የተሰኘው የሳይንስ ልቦለድ ይዘት ያለው ሰን-ስዕል (ኮሚክ) መፅሃፍ ከሌላ ዓለም የመጡ ባዕድ ፍጥረታት አፍሪካን በወረሩበት ወቅት እንዴት አፍሪካውያን ተባብረው አህጉራቸውን እንደሚያድኑ የሚተርክ ሲሆን የአድዋን ታሪክም በውስጡ ይዟል።

በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ታትሞ ለህፃናት ይቀርብ የነበረው ጀምበር አሁን ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ መግባት እንዲችል ከሰፊ ልብ፣ ትልቅ ህልም ተቋም ጋር በመሆን፣ ፈረንሳይኛ፣ ስፓኒሽ፣ ስዋሂሊ እና ግሪክን ጨምሮ በአስራ አንድ ቋንቋዎች እየተተረጎመ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ለማስተዋወቅ አቅም እንዳለው ብስራት ይገልፃል።

ጀምበርና ሌሎች አፍሪካዊ ልዕለ-ሀያል ገፀባህሪያት የሚገኙባቸው መፅሃፍት ከድህረ ገፅ ላይ ሽያጭ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህፃናት በነፃ እንዲያነቧቸው አዲስ አበባ በሚገኘው ወመዘክር ቤተመፃህፍት ይገኛሉ። ገፀባህሪያቱን በአኒሜሽን ፊልም እና በቪዲዮ ጨዋታዎች መልኩ ማቅረብ ደግሞ ቀጣዩ የብስራት ህልም ነው።

XS
SM
MD
LG