እስራኤል ጋዛን ከአየር መደብደቧን ቀጥላለች

  • ቪኦኤ ዜና

በእስራኤል የአየር ጥቃት የጋዛ ከተማ በጢስ ታፍኖ ይታያል፡፡

የእስራኤልን ተከታታይ የአየር ድብደባ ተከትሎ፣ ጋዛ፣ ዛሬ ሰኞ ማለዳ፣ በጢስ ታፍናለች፡፡

የሐማስን፣ የቅዳሜ ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ፣ የእስራኤል መንግሥት፣ ትላንት እሑድ፣ በሐማስ ላይ ጦርነት እንዳወጀ አስታውቋል። “ከበድ ያለ ወታደራዊ ርምጃ” እንደሚወሰድ፣ የእስራኤል መንግሥት አስታውቋል።

የሐማስ ሚሊሻዎች፣ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ማለዳ፣ ወረውት የነበረውን የጋዛ አቅራቢያ አካባቢን፣ እስራኤል መልሳ እንደተቆጣጠረችው፣ የአገሪቱ ወታደራዊ ዋና ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ፣ ዛሬ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።

ሌላው የእስራኤል ወታደራዊ ቃል አቀባይ የኾኑት ሌተና ኮሎኔል ጆናታን ኮርኒከስ በበኩላቸው፣ አንድ ሺሕ የሚደርሱ የሐማስ ሚሊሺያዎች፣ በጥቃቱ ወቅት ወደ እስራኤል ዘልቀው እንደገቡ ተናግረዋል፡፡ በዚኽም፣ ቢያንስ 700 የሚደርሱ ሲቪሎችንና የእስራኤል ወታደርችን ሲገድሉ፣ ከ2ሺሕ100 በላይ የሚኾኑ ሰዎችን ደግሞ አቁስለዋል።

ከሟቾቹ መካከል 250 የሚኾኑት፣ በአንድ የሙዚቃ ድግስ ላይ የነበሩና ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከታገቱት ከ100 በላይ የሚኾኑትም፣ ከዚኹ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የተወሰዱ ናቸው።

በዚኽ ጦርነት መጨረሻ ሐማስ፣ እስራኤልን የሚያጠቃበት ወታደራዊ ዐቅም እንዳይኖረው ማድረግና ጋዛን መልሶ እንዳያስተዳደር ማድረግ ነው፤”

ኮርኒከስ አክለውም፣ እስራኤል፣ 100ሺሕ ተጠባባቂ ጦሯን ለግዳጅ መጥራቷን አስታውቀዋል።

“በዚኽ ጦርነት መጨረሻ ሐማስ፣ እስራኤልን የሚያጠቃበት ወታደራዊ ዐቅም እንዳይኖረው ማድረግና ጋዛን መልሶ እንዳያስተዳደር ማድረግ ነው፤” ብለዋል ኮርኒከስ፣ የጥቃቱን ግብ ሲያመላክቱ።

በጋዛ፣ እስከ አሁን ከ400 በላይ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ተመድ በበኩሉ፣ ሁከቱ ከጀመረበት ቅዳሜ ወዲህ፣ ከ123ሺሕ በላይ ሰዎች፣ ከጋዛ ቤታቸው እንደተፈናቀሉ አስታውቋል።

እስራኤል ለጋዛ የምታቀርበውን ኤሌክትሪክ፣ ነዳጅ እና ሌሎች አቅርቦቶችን እንደምታቋርጥ፣ ቤንያሚን ናታንያሁ ተናግረዋል።

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን፣ ትላንት እሑድ፣ የእስራኤል አቻቸውን ዮአቭ ጋላንት በስልክ አግኝተው ድጋፋቸውን ገልጸውላቸዋል።

ፔንታጎን፣ ለእስራኤል የመሣሪያ ርዳታ እንደሚልክ አስታውቆ፣ አንድ የባሕር ኃይሉ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ፣ ወደ ምሥራቅ ሜዲትሬንያን እንዲንቀሳቀስ ማዘዙንም ገልጿል።