የእስራኤል ጦር በሀገሪቱ ግዛት ውስጥ የቀሩትን የሀማስ ተዋጊዎች ጠራርጎ ለማስወጣት እየሠራ እንደሆነ አስታወቀ።ጦሩ ይሄንን ያስታወቀው ታጣቂ ቡድኑ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በከፈተበት ማግስት ነው።
ጋዛ ሰርጥ ላይ መቀመጫውን ያደረገውን ታጣቂ ቡድን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ "በመቶዎች የሚቆጠሩ አሸባሪዎች" መገደላቸውን እና መማረካቸውን አንድ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣን እሁድ ዕለት ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሃይል ሀማስ ቅዳሜ ጥቃቱን በከፈተበት ጋዛ ሰርጥ አቅራቢያ በሚገኙ በርካታ ቦታዎች ላይ ውጊያ መካሄዱን አስታውቋል። ቦታዎቹ የስዴሮትን ከተማ ያካትታሉ።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ሌተናል ኮሎኔል ጆናታን ኮንሪከስ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት ቅዳሜ ዕለት ወደ እስራኤል የገቡት የሀማስ ተዋጊዎች ቁጥራቸው እስከ 1 ሺሕ 000 ሊደርስ ይችላል ።
ይህ በእንዲህ እያለ ፣ እስራኤል ስለታፈኑት ዜጎቿ ደህንነት እና ያሉበትን ስፍራ መረጃ ለማግኘት ከግብፅ እርዳታ እንደጠየቀች ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል የተባለው የዜና አውታር ዘግቧል።
ሀማስም ሆነ የእስራኤል ጦር ሀማስ የእስራኤል ወታደሮችን እና ሲቪሎችን ቅዳሜ እለት መውሰዱን ቢናገሩም የተወሰዱ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ግን እስካሁን በውል አይታወቅም።
እስራኤል እሁድ እለት በጋዛ ሰርጥ ተጨማሪ አጸፋዊ የአየር ጥቃትን ጀምራለች። የሀማስ የስለላ ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት፣ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካ እና ሁለት ባንኮች በአጸፋው ጥቃት ኢላማ ከተደረጉት መካከል እንደሆኑ የእሰራኤል የመከላከያ ኃይል ይፋ አድርጓል።
ሀማስም በበኩሉ ቴል አቪቭን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ከተሞች ሮኬቶችን በመተኮስ ሌሊቱን ጥቃቱን ቀጥሏል።
የእስራኤልን ግዛት በምድር ፣ በባህር እና አየር በኩል ጥሰው በገቡት ታጣቂዎች በትንሹ 250 እስራኤላዊያን ሲገደሉ ከ1ሺ በላይ እንደተጎዱ ተነግሯል። የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ 20 ህጻናትን ጨምሮ በጋዛ 256 ሰዎች መገደላቸውን። 121 ህጻነትን ጨምሮ 1788 ሰዎች መጎዳታቸውን እስታውቋል።
መድረክ / ፎረም