በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እየሩሳሌም የሚኖር ኢትዮጵያዊ አስተያየት


እስራኤል፣ ዌስት ባንክ እና ጋዛ፣ በምዕራብ እየሩሳሌም፣ ሃይፋ፣ ቴል አቪቭ፣ አሽዶድ፣ ሪሾን ሌዛዮን፣ ምስራቅ እየሩሳሌም፣ ጋዛ፣ ካን ዩንስ፣ ጃባሊያ እና ኬብሮን ከተሞችን ያካትታል።
እስራኤል፣ ዌስት ባንክ እና ጋዛ፣ በምዕራብ እየሩሳሌም፣ ሃይፋ፣ ቴል አቪቭ፣ አሽዶድ፣ ሪሾን ሌዛዮን፣ ምስራቅ እየሩሳሌም፣ ጋዛ፣ ካን ዩንስ፣ ጃባሊያ እና ኬብሮን ከተሞችን ያካትታል።

የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድሩት የሃማስ መሪዎች በቴል አቪቭ እና በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ በእሥራዔል ዋና ከተማ እየሩሳሌምም ውጥረት መንገሱን በከተማዋ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ነግረውናል።

"ወደ እሥራዔል የሚተኮሱ የጥቃት ሮኬቶች እየሩሳሌም ደርሰው አያውቁም ነበር" የሚለው፣ ላለፉት 25 ዓመታት በከተማዋ የኖረው ዘነበ በጋሻው፣ ትላንት ቅዳሜ መስከረም 26 2016 ዓ.ም በደረሰው ጥቃት ግን ሕዝቡ እንዲጠነቀቅ የሚደወለው የከተማው ማስጠንቀቂያ ደወል መጮሁን እና ሕዝቡ አቅራቢያው ወዳለ መጠለያ እንዲገባ መደረጉን ገልጿል።

በወቅቱ ከባለቤቱ እና ከአራት ልጆቹ ተለይቶ ሥራ ላይ እንደነበር እና ደወሉ ሲጮህ አስደንጋጭ ስሜት እንደተሰማው የሚናገረው ዘነበ፣ "በተለይ ከእየሩሳሌም ውጪ በሚኖሩ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎች የሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት፣ በተለይ ቀጥሎ ሊሆን የሚችለው ነገር የበለጠ ፍርሃት እና ጭንቀት ውስጥ ከቶናል" ብሏል።
ዘነበ በሃማስ ጥቃት የደረሰውን ጉዳት ማየት እና መስማት እጅግ እንደከበደው ይናገራል። በቴሌግራም እና በተለያዩ ማኅበራዊ ሚድያዎች የሚዘዋወሩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎችን እስካሁን እንዳልተመለከታቸውም ያስረዳል።
ከተጎጂዎቹ ወይም ከታጋቾቹ ውስጥ እስካሁን ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን እስካሁን ባያረጋግጥም "ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን እና አዛውንትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ግን ታግተዋል" ይላል።
"በተለይ እዚህ ለምንኖረው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁለት ጉዳት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉትን ነገሮች እናውቃለን፣ የሚሞቱትን የሚደርሱትን ነገሮች እናያለን። አሁን ደግሞ እዚህ የሚደርሰውን ነገር ስናይ፣ የባሰ ስሜትን ይጎዳል" ሲልም ስሜቱን ያጋራል።
ዘነበ በ25 ዓመት የእሥራዔል ኑሮው በከተማው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ዝግ ሆነው፣ ብዙ ሰው ሳይንቀሳቀስ እና፣ መንገዱ በጣም ጭር ብሎ ያየው በኮሮና ወቅት ብቻ እንደሆነ ነው የሚያስታውሰው። ከሌሎች የእሥራዔል ከተሞች በተሻለ፣ የጥቃት ስጋት ባልነበረባት እሥራዔል ግን በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚዘዋወር ሰው እንደማይታይ እና መንገዱ ባዶ መሆኑን ይገልፃል።
እሥራዔል ውስጥ ማንኛውም 18 ዓመት የሞላው ልጅ ወታደራዊ ስልጠና የሚወስድ ሲሆን፣ ምንም አይነት ሀገራዊ ችግር ሲኖር በመንግስት ጥሪ ይደረግላቸዋል። የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድሩት የሃማስ መሪዎች በእስራኤል የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ጥቃት ከከፈቱ በኃላ የመጀመሪያ መልዕክታቸውን በቴሌቭዥን ለህዝብ ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተጠባባቂ ወታደሮች እንዲጠሩ አዘዋል።
ከአራት ልጆቹ መካከል የመጀመሪያዋ ጠበቃ መሆኗን እና በመንግስት የወታደር ተቋም ውስጥ እንደምታገለግል፣ ሁለተኛ ልጁ ደግሞ ወታደር እንደሆነ እና የቅዳሜው ጥቃት በተፈፀመበት ወቅት ለእረፍት እቤት ውስጥ እንደነበር የሚገልፀው ዘነበ፣ ሁለተኛ ልጁ በድንገት ተጠርቶ መሄዱን፣ ጠበቃ ልጁ ደግሞ ከቤት እየተመላለሰች እየሠራች መሆኑን ተናግሯል። የስድስት እና የአስራ ሶስት አመት ልጆቹ ግን ትምህርት ቤት በመዘጋቱ ቤት ውስጥ ናቸው።
ዘነበ "ለኢትዮጵያም፣ ለምኖርባት ሀገርም ሰላም እንዲሆን እመኛለሁ። ክፉ ነገር የማንሰማበት ጊዜ እንዲመጣ ምኞቼ ነው" ሲል 'አስከፊ' ሲል የገለፀው ይህ ግዜ እንዲያልፍ ያለውን ፍላጎት ገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG