ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው “በምዕራቡ ጫናዎች ምክንያት ነው” ሲል የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማኅበር ያደረገው ጥናት ጠቁሟል። መንግሥት ደግሞ ሃገሪቱ ቡድኑን የተቀላቀለችው በራሷ አቅምና ፍላጎት መሆኑን መናገሩን የጥናቱን ሪፖርት ያቀረቡት ዶ/ር ደግዬ ጎሹ ተናግረዋል።
ብሪክስን መቀላቀል ሊያስገኝ ወይም ሊያሳጣ ስለሚችለው ጥቅም ባለሞያዎቹ የተከፋፈለ ሃሣብ ያንፀባረቁ ሲሆን “ብሪክስን የመቀላቀል ጉዳይ የፖለቲካ ውሣኔ ብቻ መሆን እንደሌለበት ያሳሰቡት ዶ/ር ደግዬ ሃገሪቱ ከብሪክስ ስለምታገኘው ጥቅም ጥልቅ ጥናት ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ጥምረቱን ለመቀላቀል ምን አነሣሣት?
ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የፈጠሩትንና በመሥራቾቹ ሃገሮች ስሞች ምኅፃር ብሪክስ ብለው የጠሩትን ጥምረት ለመቀላቀል ኢትዮጵያ በኦፊሴል ማመልከቷን ተከትሎ የምታገኘው ጥቅም ወይም የሚያመጣባት ጉዳት ይኖር እንደሆን ለመገምገም ጥናት ማድረጉን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች ማኅበር አስታውቋል።
የምጣኔኃብት ባለሙያዎቹ ባለፈው ሃሙስ፣ ታኅሣሥ 11 ይፋ ባደረገው የጥናት ሪፖርት ከብሪክስ አመጣጥ፣ ዓላማ፣ አሠራር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ፈትሿል። ጥናቱ፥ “በምዕራባዊያኑ ኃያላን ይዘወራሉ” ያላቸው የዓለም ባንክና ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም የሚገኙበት የኢኮኖሚ ሥርዓት “ድኆቹንና ባለጠጎቹን ሃገሮች በፍትኃዊነት አለማገልገሉ” እንደ ብሪክስ ያለ ጥምረት እንዲፈጠር ማድረጉን ይናገራል።
SEE ALSO: ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገሮች ብሪክስን ተቀላቀሉየኢትዮጵያ ጥምረቱን መቀላቀል ሊያስከትል የሚችለውን ጥቅምና ጉዳት ለመፈተሽ ማኅበራቸው 233 ባለሞያዎችን ያሣተፈ ጥናት ማድረጉን ሪፖርቱን ያቀረቡት የማኅበሩ የምርምርና ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር ዶ/ር ደግዬ ጎሹ ገልፀዋል።
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ጥምረቱን ለመቀላቀል ምን አነሣሣት? ለሚለው ጥያቄ አብዛኞቹ ባለሞያዎች በሰጡት መልስ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን እንደምክንያት ማመላከታቸውን ዶ/ር ደግዬ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባልነቷ ትጠቀማለች?”
“ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባልነቷ ትጠቀማለች?” ተብለው ከተጠየቁት የጥናቱ ተሣታፊ ባለሙያዎች ሰባ ከመቶው “አዎ፤ ትጠቀማለች” ብለው መመለሳቸውንና፤ አባልነቷ ጉዳት ያመጣባት እንደሆነ ከተጠየቁት ደግሞ፣ 69 ከመቶ ያህሉ “ከበድ ያለ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል” የሚል ሥጋት ማንፀባረቃቸውን ዶ/ር ድግዬ አሳውቀዋል።
ብሪክስ፣ አዲስ የልማት ባንክ እንደሚኖረውና የራሱን ምንዛሪ እንደሚያወጣ የገለፁት ዶ/ር ደግዬ ዋና ዓላማው በአባላቱ መካከል በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች “የራሱን ኦፊሴል ገንዘብ በመጠቀም የዶላርን የበላይነት ማስወገድ እንደሆነ” ተናግረዋል።
አብዛኞቹ ባለሞያዎች “ይህን ማድረግ ይቻላል” ብለው እንደሚያምኑ፣ ሂደቱ ግን “ከ5 እስከ 15 ዓመትና ከዚያም በላይ ሊወስድ ይችላል” ብለው እንደሚገምቱ ጥናቱ ይናገራል። ጥናቱ ይህንን ግምገማ ተንተርሶ “ኢትዮጵያ ከሁሉም ወገኖች ጋር እኩል መሥራት እንዳለባት” ይመክራል።
ነባሩ ዓለምአቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ካልሠራ አዳዲስ ጥምረቶች መፈጠራቸውና አገሮችም እነዚህን ጥምረቶች መቀላቀላቸው እንደማይቀር የጠቀሱት ዶ/ር ደግዬ ጎሹ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሃገሮች ጥቅማቸውን ግን በአግባቡ ማስላት እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
እናስ ኢትዮጵያን በባለሙያዎቹ ስሌትና ምክር ምን ይሆን ከጥምረቱ ተጠቃሚ የሚያደርጋት? ዶ/ር ደግዬ ...
የኢትዮጵያን የአባልነት ጥያቄ የተቀበለው ብሪክስ ከፊታችን ሰኞ፤ ታኅሣስ 22 / 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሙሉ አባል እንድትሆን አፅድቋል።