የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ዛሬ ባደረጉት ንግግር፣ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በአዲስ መልክ እንዲዋቀር ኢትዮጵያ እንደምትደግፍ አስታወቁ።
"የፀጥታ ምክር ቤቱን ማሻሻል ምርጫ ሳይሆን የግድ አስፈላጊ መሆኑን ኢትዮጵያ ታሰምርበታለች" ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፣ የተሻሻለ እና ለሚፈለገው አላማ መዋል የሚችል፣ ሁሉንም ያካተተ ምክር ቤት ያስፈልገናል ብለዋል። የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት የሚያከብር እና ግጭትን የሚከላከል አዲስ ዓለም አቀፍ የደህንነት ስርዓት ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።
የዓለማችንን ሰላም እና መረጋጋት ስጋት ውስጥ የሚጥሉ እና ውጥረቶችን የሚያባብዙ የፖሊሲ ምርጫዎችን በብዛት እያስተዋልን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የአፍሪካ ህብረት አባላት በጋራ በያዙት አቋም መሰረት፣ አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ማድረግ በፖለቲካውም ሆነ በመርሆ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ነው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው ሀገራት በተጠናጠል የሚያሳልፉት ማዕቀብ እና፣ ኃይል እና ማስፈራሪያን በመጠቀም የሚወሰዱ የጸጥታ ርምጃዎች የመንግስታቱን ድርጅት መርሆዎች እና ዓለም አቀፍ ህግጋትን እንደሚፃረሩ የገለፁ ሲሆን፣ "ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚወሰዱ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ትቃወማለች። ያለምንም ቅደመ ሁኔታም እንዲነሱ ትጠይቃለች" ብለዋል።
"ልዩነቶችን ለመፍታት በሉዓላዊ ሀገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ውይይት ዋና መሳሪያ ሊሆን እንደሚገባ ልናስምርበት እንወዳለን" ያሉት የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የተባበሩት መንግስታት አሁን የሚመራበት አጠቃላይ ስርዓት ማሻሻያ እንዲደረግበትም ጠይቀዋል።
በዚህ መሰረት በምኅጻረ ቃሉ “ብሪክስ” በመባል የሚታወቀው፣ የአምስት ፈጣን አዳጊ ሀገራት ጥምረት ቀዳሚ ሆኗል ያሉት አቶ ደመቀ፣ ኢትዮጵያ የቡድኑ አባል እንድትሆን በመጋበዟ አመስግነዋል።
መድረክ / ፎረም