በሱዳን በጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኅይሎች መካከል ለ20 ወራት የዘለቀውን አስከፊ ጦርነት ተከትሎ “እስከዛሬ ከተመዘገቡት ሁሉ ትልቁን ሰብአዊ ቀውስ የተሸከመች ሀገር ሆናለች” ሲል የዓለም ነፍስ አድን ኮሚቴ አመለከተ፡፡
በተቃናቃኞቹ ጀኔራሎች መካከል በቀጠለው ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ 12 ሚሊዮን የሚሆኑት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተቋሙ ዘገባ ጠቅሷል፡፡
ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን የሚጠጉት በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ መሠረተ ልማቶች በወደሙባቸው አካባቢዎች የሠፈሩ ሲሆን የጅምላ ረሃብ ሥጋትም ተጋርጦባቸዋል።
ዓለም አቀፉ ድርጅት በሱዳን ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለከባድ ረሃብ መጋለጡን ገልጾ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ሰብአዊ ቀውስ ገጥሟታል ብሏል፡፡
“ከዓለም ሕዝብ ከአንድ ከመቶ ያነሰ የሕዝብ ብዛት ያላት ሱዳን በዓለም የሰብአዊ ርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ተረጅዎች መካከል 10 በመቶውን ትሸፍናለች” ሲል እአአ የአጣዳፊ ርዳታ ፈላጊዎችን የሚከታተለውና መሠረቱን በኒው ዮርክ ያደደረገው ድርጅት እአአ በቀጣዩ 2025 የአጣዳፊ ሁኔታ ክትትል በሚያስፈልጋቸው ቀውሶች ዘገባው አስታውቋል፡፡
ከዓለም ሕዝብ ከአንድ ከመቶ ያነሰ የሕዝብ ብዛት ያላት ሱዳን በዓለም የሰብአዊ ርዳታ ከሚያስፈልጋቸው ተረጅዎች መካከል 10 በመቶውን ትሸፍናለች”
የዓለም ነፍስ አድን ኮሚቴ ዘገባ በየዓመቱ ለሰብአዊ ቀውስ ተጋላጭነት ከፍተኛ ሥጋት ያለባቸውን 20 ሀገራት ለይቶ በማጉላት የሚያሳይ ሲሆን ሱዳን ለሁለት ተከታታይ ዓመታት በቀዳሚነት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡
በሀገሪቱ በጠቅላላው 30.4 ሚሊዮን ሰዎች በሰብአዊ እርዳታ ፈላጊዎች መሆናቸውን የገለጸው ኮሚቴው የተረጅዎችን ቁጥር መመዝገብ ከጀመረ ወዲህ ይህ “ከምንጊዜውም ትልቁ የሰብአዊ ቀውስ” መሆኑን ገልጿል።
ኮሚቴው በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ወደ 305 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ የሚሹ መሆኑን ዘግቧል፡፡ ከእነዚህ 82 ከመቶ የሚሆኑት በኃይል በተያዙት የፍልስጤም ግዛቶች፣ ሚያንማር፣ ሦሪያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሊባኖስ በመሳሰሉት ክትትል ያስፈልጋቸዋል ተብለው በተመዘገቡ የቀውስ አካባቢዎች እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የዓለም ነፍስ አድን ኮሚቴ ኃላፊ ዴቪድ ሚሊባንድ ‘ዓለም እሳት ላይ ነች’ ይህ በመቶ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የዕለት ተዕለት እውነታ እንደሆነ ግልጽ ነው።” ብለዋል፡፡
ሚሊባንድ አክለውም "ዓለማችን በሁለት ካምፖች እየተከፈለች ነው፤ ባልተረጋጋ እና ግጭት ባለበት ቦታ በተወለዱት እና በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የመኖር እድል ባላቸው መካከል" ማለታቸውን ኤኤፍፒ ጠቅሷል፡፡