ቤልጂግ ብራሰልስ ውስጥ ባለፈው ሳምንት የደረሰውን የብዙ ሰው ህይወት ያጠፋ የሽብርተኛ ጥቃት ተከትሎ አውሮፓ ውስጥ የስለላ መረጃዎችን መጋራትን አስመልክቶ የተሻለ ስራ መሰራት አለበት ይቻላልም ስትል ዩናይትድ ስቴትስ አሳሰበች።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጆሽ እርነስት ሲናገሩ በብራስልስ አውሮፕላን ጣቢያ እና የመሬት ውስጥ ባቡር ላይ የደረሱት ጥቃቶች መሰረታዊ የስለላና የብሄራዊ ጸጥታ አሰራር ደምቦች መከበር እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ነው ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ቢልጂየም የሽብር ጥቃቶቹን አስመልክታ በምታደርገው ምርመራ የምትረዳ መሆኑን ቃል አቀባዩ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ትናንት የቤልጂግ ባለስልጣናት የሽብር ጥቃቱ ዋና ተጠርጣሪ ተብሎ በስፋት በዘገባዎች የቀረበውን ግለሰብ ታስሮ የሚቆይበት ምክኒያት ስላላገኘን ለቀነዋል ብለዋል። ፈይሰል ሲ የተባለው ሰው ቀደም ብሎ የሽብርተኛ ቡድን አባል በመሆን፣ የሽብር ግድያ በመፈጸምና፣ ለመፈጸም በመሞከር ክስ ቀርቦበት ነበር።
ሰውየው በብረሰልሱ አውሮፕላን ጣቢያ አጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ፍንዳታ ካደረሱት ከሁለቱ ሰዎች ጋር ከፍንዳታው ጥቂት ቀደም ብሎ በአውሮፕላን ጣቢያው የጸጥታ ጥበቃ ቪዲዮ የታየው ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ዘገባዎች መሰራጨታቸው ይታወሳል።