በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሎስ አንጀለስ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ፍልስጥኤማውያንን በመደገፍ የተሰበሰቡትን ተቃዋሚ ሰልፈኞች ፖሊስ መበተን ጀመረ


በካልፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሎስ አንጀለስ ግቢ የፍልስጤማውያን ደጋፊዎች በአንድ ወገን እና የእስራኤል ደጋፊዎች በሌላ ሆነው ተጋጭተዋል፣ ፖሊስ መሃል ገብቶ ለያይቷቸዋል፤ እአአ ግንቦት 1/2024
በካልፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሎስ አንጀለስ ግቢ የፍልስጤማውያን ደጋፊዎች በአንድ ወገን እና የእስራኤል ደጋፊዎች በሌላ ሆነው ተጋጭተዋል፣ ፖሊስ መሃል ገብቶ ለያይቷቸዋል፤ እአአ ግንቦት 1/2024

ሎስ አንጀለስ ከተማ በሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ግቢ ድንኳን ተክለው የሰፈሩትን የፍልስጥኤማውያን ደጋፊ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ፖሊስ እየበተነ ነው፡፡ ፖሊሶች ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ስፍራውን እንዲለቅቁ ትዕዛዝ ከሰጡ በኋላ ሰልፈኞቹ ያቆሟቸውን አጥሮች እያፈረሱ ብዙዎቹን በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል፡፡

የፖሊሶቹ እርምጃ ለበርካታ ሰዓታት የቀጠለ ሲሆን መጀመሪያ ላይ የተቃዋሚዎቹ ድንኳኖች አቅራቢያ ከቆሙ በኋላ ለአጭር ጊዜ ገፍተው ገብተው ወዲያው ሲያፈገፍጉ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በሆታ አጅበዋቸዋል፡፡ ከአንድ ሰዓት በኋላ የተላከው ብዛት ያለው የፖሊስ ኅይል የተቃዋሚዎቹን አጥሮች እና ድንኳኖች አፈራርሷል፡፡

የብረት ቆብ እና ፊት መሸፈኛ የለበሱት እና ቆመጥ የያዙት ተቃዋሚዎቹን እየገፈተሩ ማስወጣት ሲጀምሩ ዩኒቨርስቲው እስራኤልን በሚደግፍ ድርጊት ከመሳተፍ እንዲርቅ በመጠየቅ የተሰበሰቡት ተቃዋሚ ሰልፈኞች “ይህ ሰላማዊ ሰልፍ ነው” በማለት መፈክር አሰምተዋል፡፡

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲው ተቃውሞ በሀገሪቱ ዙሪያ ፍልስጣኤማውያንን በመደገፍ እየተካሄዱ ካሉት የተቃውሞ ሰልፎች አንዱ ሲሆን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል፡፡ በኒው ሀምሻይር ግዛት ዳርትመዝ ኮሌጅ ደግሞ ትላንት ረቡዕ ማታ ፖሊሶች የተቃዋሚ ሰልፈኞች ድንኳኖችን ያነሱ ሲሆን የታሰሩ ሰዎችም አሉ፡፡ ቴክሳስ ዳላስ ከማ በሚገኘው የቴክሳስ ዩኒቨርስቲም ፖሊሶች ተመሳሳይ እርምጃ ወስደው በትንሹ 17 ሰዎች አስረዋል፡፡ በኒው ዮርክ ፎርደም ዩኒቨርስቲም ቢያንስ 15 ሰዎች ታስረዋል፡፡

በሚኔሶታ ዩኒቨርስቲም የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች ትላንት ከዩኒቨርስቲው ተጠባባቂ ፕሬዚደንት ጋራ መነጋገራቸውን ገልጸው ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በኒው ዮርክ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አስተዳዳሪዎች እየተገባደደ ያለው የትምህርት ሴሚስተር በርቀት እንደሚካሄድ ትላንት አስታውቀዋል፡፡ ፖሊሶች በስተያ ማክሰኞ በዚያ ድንኳን ተክለው የሰፈሩትን የተቃውሞ ሰልፈኞች የበተኑ ሲሆን 300 የሚሆኑ ሰዎችን አስረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ረቡዕ በፍልሥጥዔም አገረ መንግሥትነት ጉዳይ በተካሄደ የተ መ ድ ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ላይ የእስራኤል አምባሳደር ባደረጉት ንግግር የተማሪዎቹን ተቃውሞ አውግዘዋል፡፡ “ ሃማስ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሚደበቅ እናውቃለን ፡፡ ያላወቅነው የሚደበቀው ጋዛ ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ሃርቫርድ እና ኮሎምቢያን በመሳሰሉ ምርጥ ዩኒቨርስቲዎችም ጭምር መሆኑን ነው” ብለዋል፡፡

የኋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን ፒዬር በበኩላቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል “ህግ ባከበረ እና በሰላማዊ መንገድ እስከተካሄደ ድረስ ሰዎች ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረግ መብታቸው ነው” ብለዋል፡፡ የባይደን አስተዳደር ምንም ዓይነት ጸረ ሴማዊ ንግግር እና ጥላቻ እንደሚቃወም ቃል አቀባይዋ አክለው ገልጸዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG