በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ በመርዓዊ ከተማ በተፈጸመው ግድያ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀች


መርዓዊ ከተማ
መርዓዊ ከተማ

በኢትዮጵያ አማራ ክልል 80 ሲቪሎች መገደላቸውን አንድ የአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅት እንዳረጋገጠ መግለጹን ተከትሎ፣ የአሜሪካ መንግስት ምርመራ እንዲደርግ ጠይቋል።

በሰሜን ጎጃም ዞን በመርዓዊ ከተማ በክልሉ የሚገኙ ታጣቂዎች ከፌዴራል ኃይሎች መጋጨታቸውን ተከትሎ፣ የፌዴራሉ ኃይል ዓባላት ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ ከ50 በላይ ሲቪሎች መግደላቸውን የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች መግለጻቸው ይታወሳል።

“ከአማራ ክልል መርዓዊ ከተማ የወጡትና ሲቪሎችን ኢላማ ያደረጉ የግድያ ሪፖርቶች፣ የአሜሪካ መንግስትን በእጅጉ ያሳስበዋል” ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ዛሬ ዓርብ ገልጸዋል።

የሰብዓዊ መብት መርማሪያዎች ካለገደብ በአካባቢው ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ግድያ የፈጸሙትም ለፍርድ እንዲቀርቡ”

“የሰብዓዊ መብት መርማሪያዎች ካለገደብ በአካባቢው ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ግድያ የፈጸሙትም ለፍርድ እንዲቀርቡ” ሲሉ አምባሳደሩ ጥሪ አድርገዋል።

በመርዓዊ ከተማ ተፈጸመዋል የተባሉት ግድያዎች፣ በውስጥ ግጭቶች በታመሱት ከአማራም ሆነ ከሌሎች ክልሎች የተሰሙትን “አስደንጋጭ የሁከት ሪፖርቶችን” ተከትለው የመጡ መሆኑን አምባሳደር ማሲንጋ አውስተዋል። በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎችም ክልሎች የታዩ ሁከቶችን እና በደሎችን አስመልክቶ የወጡ ሪፖርቶች፣ የመንግስትንም ሆነ ከመንግስት ውጪ ያሉ ኃይሎችን በተመሳሳይ ተጠያቂ እንዳደረጉ አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

በመርዓዊ ከተማ ባለፈው ሳምንት የነበረውን ግጭት ተከትሎ ቤት ለቤት በመዘዋወር እና በጅምላ በተፈፀመ ግድያ ከ80 በላይ ሲቪሎች እንደተገደሉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ባለፈው ማክሰኞ አስታውቋል፡፡

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚታዩ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በዚህ ሳምንት ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG