በሱዳን በሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች መካከል ያለው ጦርነት መቀጠሉን ተከትሎ፣ ልዩ ልዩ ሀገራት፣ ዜጎቻቸውንና ዲፕሎማቶቻቸውን ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ማስወጣታቸውን ቀጥለዋል። መብራት፣ ውኃ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠባቸው በካርቱም እና አካባቢዋ የሚኖሩ ሱዳናውያን ደግሞ፣ ከውጊያው ለማምለጥ አደገኛ በኾኑ ጎዳናዎች፣ በመኪና እና በእግር ለመውጣት ጥረት እያደረጉ ናቸው።
በሱዳን ጦር ኃይሎች እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መካከል ልዩ እየተካሔደ ባለው ጦርነት፣ 264 ሲቪሎችን ጨምሮ እስከ አሁን ከ420 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ3ሺሕ700 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተገልጿል። በሱዳን በሁለቱ ጄነራሎች እና አጋሮቻቸው መካከል የሚካሔደው ውጊያ ቀጥሎ 10ኛ ቀኑን በአስቆጠረበት ኹኔታ፣ ልዩ ልዩ የውጭ ሀገራት፣ ዲፕሎማቶቻቸውንና ዜጎቻቸውን እያስወጡ ነው።
ከአንድ ሳምንት በላይ በዘለቀው ጦርነት ምክንያት፣ የውጭ ዜጎችን ከሱዳን ለማውጣት አስቸጋሪ ቢኾንም፣ ባለፈው እሑድ ጠዋት ለመጀመሪያ ጊዜ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ኃይሎች፣ 70 የኤምባሲ ሠራተኞችን ከካርቱም አውጥተዋል። በሱዳን ቢያንስ 16ሺሕ የአሜሪካ ዜጎች እንደሚኖሩ ቢገለጽም፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በሺሕዎች የሚቆጠሩትን ዜጎች፣ በመንግሥት የተቀናጀ መንገድ ማስወጣቱ ያለውን አደገኛነት አመልክተዋል።
ከካርቱም የተነሡት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች፣ ወደ ኢትዮጵያ መወሰዳቸውን ያመለከቱት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለአደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል። “ለሥራችን ስኬት ወሳኝ የኾኑትን ጅቡቲን፣ ኢትዮጵያንና ሳዑዲ አረቢያን አመሰግናለሁ፤” ያሉት ባይደን፣ “በድፍረት እና በሞያዊ ብቃት” ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ነበር ባሏቸው የኤምባሲያቸው ሠራተኞችም እንደሚኮሩ ገልጸዋል።
ወደ 100 የሚጠጉ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች፣ ኤምኤች 47 በተሰኙ ሦስት ሄሊኮፕተሮች በመታገዝ ወደ 70 የሚጠጉ የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞችን በማስወጣት ኢትዮጵያ ውስጥ አካባቢው ወዳልተጠቀሰ ስፍራ የተወሰዱ ሲኾን፣ ኢትዮጵያ፥ ተጨማሪ የበረራ እና የነዳጅ አቅርቦት ድጋፍ መስጠቷን፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ፣ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የሚካሔደውን ግጭት የሸሹ የመጀመሪያዎቹ የሶማልያ ዜግነት ያላቸው 27 ሰዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ የሶማልያ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ሶማሌዎቹ፣ የድንበር ከተማ የኾነችውን መተማ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ አልፈው መግባታቸውንና በኢትዮጵያ ወታደሮችም መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው፣ የአሜሪካ ድምፅ የሶማልኛ ቋንቋ አገልግሎት ዘግቧል።
ካርቱም የሚገኘው የሶማልያ ኤምባሲ፣ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጥረት የሚያደርጉ ተጨማሪ ሶማሌዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እያቀኑ እንደኾነ ገልጾ፤ በሱዳን የሶማልያ አምባሳደር የኾኑት መሐመድ ሼክ ኢሳቅ እና የሶማልያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት፣ ሶማሌያውያን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበትን ኹኔታ፣ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋራ እየተነጋገሩበት መኾኑን ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል።
እንግሊዝን ጨምሮ ለሌሎች የዓለም ኃያል ሀገራትም እንዲሁ፣ ዲፕሎማቶቻቸውንና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ሲኾን፣ ፈረንሳይ እና ጣሊያን፣ የራሳቸውን ዜጎች ብቻ ሳይኾን፣ መውጣት የሚፈልጉ የሌሎች ሀገራትንም ዜጎች እንደሚያስወጡ ገልጸዋል።
ጀርመንም እንዲሁ፣ ባለፈው ሰኞ ጠዋት፣ 101 የጀርመን ዲፕሎማቶችን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ሌሎች የአጋር ሀገራት ዜጎችን የያዘ ወታደራዊ አውሮፕላን፣ ከሱዳን ተነሥቶ፣ በጆርዳን በኩል በርሊን ማረፉን አስታውቃለች፡፡ ሌሎች 311 ሰዎችም፣ ወደ ጆርዳን ተወስደው ለቀጣዩ ጉዞአቸው ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን አመልክታለች።
የኔዘርላንድ፣ ጣሊያንና የስፔይን አየር ኃይሎችም፤ ከአውሮፓ፣ ከእስያ፣ ከሰሜን አሜሪካ እና ከአፍሪካ የተውጣጡ ዜጎችን ከሱዳን ማስወጣታቸውን አስታውቀዋል።
ከ10 ሺሕ በላይ ዜጎቿ በሱዳን እንደሚኖሩ ያስታወቀችው ግብፅ በበኩሏ፣ ከካርቱም ውጪ ያሉ ዜጎቿ ከሀገሪቱ ለመውጣት ፖርት ሱዳን ወደሚገኘው የቆንስላ ጽ/ቤት እና በስተሰሜን ወደሚገኘው ዋዲ ሃልፋ እንዲሔዱ አሳስባለች፤ ሲል፣ የሀገሪቱ መንግሥት የዜና ማሠራጫ የኾነው፣ ሜና የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዱጃሬክ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የተቋሙ ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው፣ ከሱዳን መውጣት እና ደኅንነታቸው ወደሚጠበቅበት ቦታ መዘዋወራቸውን ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል።
ዋና ጸሐፊው፣ “ሁለቱ የሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች፣ በአስቸኳይ ጦርነቱን እንዲያቆሙና አጣብቂኝ የገቡ ሰላማዊ ዜጎች ከግጭቱ አካባቢ እንዲወጡ እንዲፈቅዱ፣ አሁንም ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፤” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት፥ ውጥረቱን ለማርገብ እና ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርስ ለማድረግ ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል መካከል የሚካሔደውን ግጭት ሸሽተው፣ ወደ ጎረቤት ሀገር ቻድ የሚገቡትን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ለመቀበል እየተዘጋጀ መኾኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል። የተቋሙ የቻድ ተወካይ ፒየር ኾኖራት ለሮይተርስ እንዳስታወቁት፣ በሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ባለው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ከ10ሺሕ እስከ 20ሺሕ የሚደርሱ ሱዳናውያን ወደ ቻድ ገብተዋል።
“ቁጥራቸውን ለመገመት አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት፣ ከ10 እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ ስደተኞች በቻድ ይገኛሉ፤” ያሉት ሆኖራት፣ “ሌሎች ስደተኞችም እየመጡ እንደኾነ ርግጠኞች ነን። እጅግ የተወሳሰበ ኹኔታ ነው የሚኖረው። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቢያንስ 100ሺሕ ስደተኞችን ለመቀበል እየተዘጋጀ ነው። ይህ የመጀመሪያው ዙር ነው። ነገር ግን ተጨማሪዎች ይኖራሉ፤” ሲሉ አብራርተዋል።
ሆኖራት እንዳሉት፣ ዐዲስ የሚገቡት ስደተኞች፣ ከዚኽ ቀደም በተከሠቱ ግጭቶች፣ ከሱዳን ተሰድደው በቻድ ድንበር አካባቢ ባሉ 14 መጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ 400 ሺሕ ሱዳናውያንን ቁጥር ያሳድጉታል።
“በጣም አሳፋሪ ነው። በጣም ብዙ ሕፃናት ድንበር አቋርጠው ከሴቶች ጋራ በዛፍ ሥር ተቀምጠው ስናይ በጣም አስደንጋጭ ነው። በቦታው ሌላ ምንም ነገር የለም። ያስጨንቃል፤ ያን ማየት ልብ ይሰብራል። በዚያ ላይ በጣም ብዙ ተሠቃይተዋል። አንዳንዶቹ አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ቤታቸው ተቃጥሎባቸዋል፤ መንደሮቻቸው ወድመዋል፤ የአንዳንዶቹ ጎረቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተዘርፈዋል።”
በዋና ከተማዋ ካርቱም ተስፋ የቆረጡ ነዋሪዎች፣ አሁንም በቦምብ ድብደባ እና ከተማዋን በሚዘዋወሩ ተዋጊዎች መሀል አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ በየመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተደብቀዋል። አሁንም ከግጭቱ መውጣት ያልቻሉ በርካታ የውጭ ሀገራት ዜጎች፣ የኤምባሲ ሠራተኞች፣ የርዳታ ሠራተኞች እና በካርቱም እና በሌሎች አካባቢዎች ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችም እንዲሁ፣ አሁንም አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው።
/ዘገባው በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ፣ ሮይተርስ እና አሶሽየትድ ፕሬስ የተጠናቀረ ነው። ስመኝሽ የቆየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች/