በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሀገራት ውጊያው ከቀጠለባት ከሱዳን ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን እያስወጡ ናቸው


ዮርዳኖሳውያን፣ አማን ዮርዳኖስ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ሲደርሱ
ዮርዳኖሳውያን፣ አማን ዮርዳኖስ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ሲደርሱ

ሱዳን ውስጥ በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል ውጊያው ቀጥሏል፡፡ የተለያዩ ሀገሮች ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት እየተጣደፉ ናቸው፡፡ በአውሮፕላኖች እና በመኪና አጀብ ዚጎቻቸውን በማስወጣት ላይ ካሉት ሀገሮች መካከል ካናዳ፡ ግብጽ፡ ፈረንሳይ፡ ጀርመን፡ ጣሊያን ስዊድን እና ዩናይትድ ስቴትስ ይገኙባቸዋል፡፡

እስካሁን በውጊያው የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ420 ያለፈ ሲሆን በሺዎች የተቆጠሩ ቆስለዋል፡፡

መብራት ውሃ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠባቸው እና የሚደርስላቸው የሌላቸው ሱዳናውያን ደግሞ አንዳንዶቹ ከውጊያው ለማምለጥ አደገኛ በሆኑ ጎዳናዎች በመኪናም በእግርም ለመውጣት እየሞከሩ ናቸው፡፡

በተያያዘ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ የዐለም አቀፍ ልማት ተራድዖ (ዩኤስኤአይዲ) የአጣዳፊ አደጋ ምላሽ ሰጪ ባለሙያዎች ቡድን ወደሱዳን መላኩን የተቋሙ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ትናንት ዕሁድ አስታውቀዋል፡፡ ኤክስፐርቶቹ መጀመሪያ ስራቸውን የሚያካሂዱት ከኬኒያ እንደሚሆን ዋና አስተዳዳሪዋ ገልጸዋል፡፡

“ዩናይትድ ስቴትስ በተዋጊዎቹ ወገኖች ፍልሚያ መካከል የተጠመደውን የሱዳንን ህዝብ ለመርዳት እንቅስቃሴዋን በምጠናከር ላይ ነች” ያሉት ሳማንታ ፓወር “ዳርት” የሚል የአህጽሮት መጠሪያ የተሰጠው የባለሙያዎች ቡድን “ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ችግሮችን በመለየት አጣዳፊ እርዳታ ለሚያፈልጋቸው ሰዎች ደህንነቱ በጠበቀ መንገድ ህይወት አድን ዕርዳታዎችን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ለማድረስ ከዐለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ከዐለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር አብሮ ይሰራል “ ብለዋል፡፡

“ሱዳናውያን ቤተሰቦች የራማዳን ጾም ማብቂያ የኢድ በዐላቸውን ሊያከብሩ ሲገባ በዐሉን በሽብር አሳልፈዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡

ከሱዳን ህዝብ አንድ ሦስተኛውን የሚይዙት ወደ16 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ውጊያው ከመጀመሩም አስቀድሞ የሰብዐዊ ዕርዳታ ጠባቂ እንደነበሩ የገለጹት ሳማንታ ፓወር ውጊያው ፊትም የነበረውን ከባድ እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG