በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የርዳታ ምግብ ሥርጭቱን ማቆሙን አስታወቀ


የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የርዳታ ምግብ ሥርጭቱን ማቆሙን አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:07 0:00

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ የርዳታ ምግብ ሥርጭቱን ማቆሙን አስታወቀ

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም(WFP)፣ ለኢትዮጵያ ተጎጂዎች ሲያሠራጭ የቆየውን የምግብ ርዳታ፣ “ስርቆት በመንሰራፋቱ” ምክንያት ለጊዜው ማቆሙን፣ ዛሬ አስታወቀ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የርዳታ ምግብ የማቆም ውሳኔውን ይፋ ያደረገው፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ተመሳሳይ ርምጃ መውሰዷን፣ በዩኤስኤአይዲ በኩል ካሳወቀች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ውሳኔን ተከትሎ፣ በሕዝብ ብዛት ከአፍሪካ ሁለተኛ በኾነችው ሀገር፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የበለጠ ሊጨምር ይችላል፤ የሚል ስጋት አይሏል።

ውሳኔውን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዲሬክተር ሲንዲ ማኬይን፣ “የምግብ ርዳታ ለተረጂዎች እንዳይደርስ ማድረግ በፍጹም ተቀባይነት የለውም፤” ያሉ ሲኾን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሓላፊነት ያለባቸውን ለማጣራትና ተጠያቂ ለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነት እንደሚያደንቁም ገልጸዋል።

በአፍሪካ ቀንድ፣ ባለፉት ዐሥርት ዓመታት ባልታየው ድርቅ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀውና በ10ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ባጠፋው ግጭት ምክንያት፣ በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ ሰዎች፣ የምግብ ርዳታ ጠባቂዎች ናቸው፡፡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በነዚኽ ሁለት ቀውሶች ምክንያት የተጎዱ፣ ሰባት ሚሊየን ሰዎችን ሲረዳ ቆይቷል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም(WFP) እና የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት(USAID)፣ ለውሳኔያቸው ምክንያት በኾነው፣ “የርዳታ ለተጎጂው አለመድረስ” ጉዳይ፣ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ የዜና አውታሮች የተመለከቱትና ለለጋሽ አካላት የተሠራጨው መግለጫ፣ በፌደራል እና በክልል መንግሥታት ባለሥልጣናት የተቀናጀ የጥቅም ትስስር፣ የርዳታ ምግብ፣ ወደ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ክፍሎች እንደሚዘዋወር አመልክቷል።

በዋናነት የሚያሳስበን፣ በእኛ ድጋፍ ላይ ጥገኛ የኾኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ ረኀብተኞች ጉዳይ ነው፤ ያሉት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዲሬክተር፣ በተቻለ ፍጥነት ሥራችንን ለመቀጠል፣ ከሁሉም አጋሮቻችን ጋራ ያለመታከት እንሠራለን፤ ብለዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም፥ ለሕፃናት፣ ለነፍሰ ጡሮች እና ለሚያጠቡ እናቶች የሚደረግ የተመጣጠነ ምግብ ርዳታ፣ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብሮች፣ የአርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ዐቅም ለመገንባት የሚደረጉ ድጋፎች ግን ሳይቋረጡ እንደሚቀጥሉ በመግለጫው አስታውቋል።

በሮይተርስ የተጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG