በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምዕራብ ወለጋ ዞን የተፈፀመው የጅምላ ግድያ በአስቸኳይ እንዲጣራ ተመድ ጠየቀ


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት

በምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ምዕራብ ወለጋ ዞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጣን፣ ገለልተኛ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ እንዲያካሂድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሸሌት አሳሰቡ።

ባሸሌት ዛሬ ባወጡት መግለጫ "ቶሌ በተሰኘው መንደር በደረሰ ጥቃት የተፈፀመው ትርጉም የማይሰጥ ግድያ እና ሰዎች በግዳጅ ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው አሰቅቆኛል" ብለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ የዓይን እማኞችን አነጋግሮ ባሰባሰበው መረጃ፣ ሰኔ አስራ አንድ ቀን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ የታጠቁ ሰዎች፣ በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች በሚኖሩበት ቶሌ መንደር በመሄድ በዘፈቀደ ባካሄዱት ተኩስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ አብዛኞቹ ሴቶች እና ህፃናት ናቸው። በተጨማሪም ቢያንስ 2ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዋል። አራት ሰዓት በፈጀው በዚህ ጥቃት ታጣቂዎቹ በርካታ መኖሪያ ቤቶችንም አቃጥለዋል።

ባሸሌት በመግለጫቸው "የኢትዮጵያ መንግሥት ጥቃቱን ለማጣራት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ጥቃት የደረሰባቸው እና ቤተሰቦቻቸው እውነቱን እንዲያውቁ ማድረግ፣ ፍትህ እና ካሳ ማግኘታቸውን እንዲሁም አጥፊዎቹ ተጠያቂ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለበት" ብለዋል።

በተጨማሪም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በጥቃቱ ወቅት ታግተው መወሰዳቸውንና እስካሁን ያሉበት እንደማይታወቅ ያስታወቁት ከፍተኛ ኮሚሽነሯ "ባለሥልጣናት አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የታገቱት ሰዎች ነፃነታቸውን እንዲያገኙ እንዲያደርጉ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች እየጨመረ የመጣውን ውጥረት እና ሁከት ትከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ህብረተሰቡ ለመኖር ያለውን መብት እንዲያረጋግጥ ሲሉ ከፍተኛ ኮሚሽነሯ ጨምረው አሳስበዋል።

XS
SM
MD
LG