ዋሽንግተን ዲሲ —
ምግብና መድኅኒት የጫኑ ካምዮኖች ሦርያ ውስጥ በመንግሥትና በተቃዋሚ ሃይሎች ተከበው ወደ ነበሩት ቦታዎች ለመግባት ዛሬ ይነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ረድኤት እንዳያገኙ በመንግሥትና በተቃዋሚ ሃይሎች ከበባ ታግደው ቆይተዋል።
የረድኤት አቅርቦት የሚገባው በሦርያና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መካከል በተደረገው ስምምነት መሰረት ነው። የእርዳታው አቅርቦት ወደ ሰባት የሀገሪቱ አከባቢዎች ይገባል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ የሶርያ ልዑክ ስቴፋን ደ ምስራታ(Staffan de Mistura) ትላንት ደማስቆ ውስጥ ስብሰባዎች ካደረጉ በኋላ እርዳታ የማቀበሉ ተግባር የሦርያ መንግስት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሕዝቡ እርዳታ እንዲያቀርብና ከሕዝቡ ጋር እንዲገናኝ የማድረግ ፍላጎቱ ምን ያህል እንደሆነ ይፈትናል ብለዋል።
የሦርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ሀገሪቱ ለሕዝቧ የሚያስፈልገውን ነገር ለመፈጸም ግዴታዋ የማንም አስታዋሽነት አያስፈልትም ሲሉ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሉዑኩ አባል ዛሬ ምላሽ ሰጥቷል።