በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሰባቱ የተመድ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ወጡ


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ

በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲወጡ የታዘዙት ሰባቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ሃገሪቱን ለቅቀው መውጣታቸውን ዛሬ የመንግሥታቱ ድርጅት አረጋገጠ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድርጅት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃክ ባለሥልጣናቱ ለደህነታቸው ሲባል ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።

ፋርሃን ሃክ ከጋዜጠኞች ለተነሳ ቀጣይ ጥያቄ በሰጡት መልስ "እኛ ቅድሚያ ትኩረት የምንሰጠው ሰራተኞቻችን ደህንነታቸው በሚጠበቅበት ሁናቴ ስራቸውን መስራት መቻላቸውን ማረጋገጥ ነው፥ ያን ማድረግ የማንችል ሲሆን ደግሞ ሌላ እርምጃ መውሰድ አለብን " ብለዋል።

ባለፈው ሃሙስ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰባቱን የተመድ ባለሥልጣናት በሰባ ሁለት ሰዓት ውስጥ እንዲወጡ ትዕዛዝ የሰጠው።

የመንግሥታቱን ድርጅት ባለሥልጣናት "በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እንዲሁም መንግሥቱ በአሸባሪነት ለፈረጀው ለትግራይ ነጻ አውጭ ግንባት ህወሓት እርዳታ እና የቴሌኮሙኒኬስን መሳሪያዎች በማቀበል ከሱዋቸዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናቱን ፔርሶና ኖን ግራታ (ተቀባይነት የሌላቸው ሰዎች) ብሎ እንዲወጡ በማዘዝ የወሰደው እርምጃ "አስደንግጦኛል" ሲሉ ሃሙስ ዕለት የተናገሩ ሲሆን በማግስቱ ዐርብ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ ተነጋግረዋል፤

እንዲወጡ ከታዘዙት ባለሥልጣናት መካከል የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊው እና የህጻናት መርጃ ድርጅቱ የዩኒሴፍ ተወካይ ይገኙባቸዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት በዓለም አቀፍ ኮንቬንሲኖች እና በድርጅታችን ቻርተር ሰራተኞቻችን ያለመከሰስ መብታቸውን የተጠበቀ በመሆኑኢትዮጵያ የምታስወጣበት ህጋዊ መሰረት የላትም ብለዋል። በሰራተኞቻችን ከወገንተኝነት ነጻነት ሙያቸውን አክባሪነት እንተማመንባቸዋለን ሲልም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ድርጅቱ እንዲወጡ በታዘዙት ሰራተኞቹ ምትክ ሌሎች መላክ ይችላል ሲል ያስታወቀ ቢሆንም የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ በአሁኑ ሰዐት ያን ለማድረግ እቅድ የለንም ብለዋል።

XS
SM
MD
LG