በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ የተመድ ሰባት ባለሥልጣናት እንዲወጡ አዘዘች


ፎቶ ፋልይ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ
ፎቶ ፋልይ፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ

ጉቴሬሽ ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት ባለሥልጣናት በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሃገር እንዲወጡ መወሰኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/ እና የጅርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች የኢትዮጵያ ቢሮዎች ኃላፊዎችንና አንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አንድ የቡድን ኃላፊን ጨምሮ ሰባቱ የድርጅቱ ሠራተኞች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል በሚል መንግሥት “ተቀባይነት የሌላቸው ግለሰቦች” ወይም የ“ፔርሶና ኖን ግራታ” ውሳኔ ያወጣባቸው መሆኑን አመልክቷል።

መሥሪያ ቤቱ “ፔርሶና ኖን ግራታ” የተላለፈባቸውን ሠራተኞች ስሞች ዝርዝር ያወጣ ሲሆን በሰባ ሁለት ሰዓታት ውስጥ ከሃገር እንዲወጡ መወሰኑንም አስታውቋል።

ይህንኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን ሰባቱን ባለሥልጣናት ከሃገር የማስወጣት እርምጃ አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ማምሻውን ባወጡት መግለጫ ውሳኔው ያስደነገጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

“የመንግሥታቱ ድርጅት እንቅስቃሴዎች ሁሉ በሰብዓዊነት፣ ባለመወገን፣ በገለልተኛነትና በነፃነት አስኳል መርኆች የሚመሩ ናቸው” ብለዋል ዋና ፀሃፊው።

ጉቴሬሽ በመቀጠልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብን፣ መድኃኒት፣ ውኃ፣ የንፅህና መጠበቂያ አቅርቦቶችን ጨምሮ ህይወት አድን እርዳታ እጅግ ለሚስፈልጋቸው ሰዎች እያደረሰ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የድርጅታቸው ሠራተኞች ይህንኑ እያከናወኑ ስለመሆናቸው ሙሉ መተማመን እንዳላቸው ገልፀዋል።

“ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልገውን የኢትዮጵያ ህዝብ ለማገዝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቁርጠኛ ነው” ያሉት አንቶኒዮ ጉቴሬሽ የተጠቀሱት የድርጅቱ ሠራተኞች አስፈላጊውን ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል በሚል ተስፋ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG