በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እንዲወጡ በተወሰነባቸው ባለሥልጣናት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ አውጥቷል


የኢትዮጵያ መንግሥት ከሃገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ያወጣባቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች የሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ አውጥቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሃገር እንዲወጡ ትዕዛዝ ያወጣባቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት ባለሥልጣናትና ሠራተኞች የሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ አውጥቷል።

ኢትዮጵያ ከመሥራች አባልነቷ አንስቶ ለመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር መከበር ያላትን ቁርጠኛነት በመናገር የጀመረው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቷ የወጣው ማብራሪያ ህይወት አድን እርዳታ እየሰጡ ለብዙ ዓመታት ለቆዩ የድርጅቱ ተቋማት ሁሉ ምሥጋናና አድናቆት እንዳለው አስታውቋል።

ማብራሪያው በመቀጠልም ትግራይ ውስጥ እርዳታ ለማድረስ የተጠናከረ የማስተባበሪያ አሠራር የመግባቢያ ሠነድ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ጋር ኅዳር 20/2013 ዓ.ም. መፈረሙን አስታውሶ አሁን ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘ ግን አንዳንድ የድርጅቱ ሠራተኞች ከመግባቢያ ሠነዱና ከመንግሥታቱ ድርጅት ተያያዥ መርኆች ጋር በሚጣረስ ሁኔታ ተልዕኳቸውን በነፃነትና በገለልተኛነት እንደማይወጡ መንግሥቱ ከኀዘን ጋር መታዘቡን አመልክቷል።

“ብርቱ ናቸው” ያላቸውን ጥሰቶች ለመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ለሌሎችም ዓለምአቀፍ አጋሮች በበዙ አጋጣሚዎች ቢያሳውቅም መፍትኄ አለመሰጠቱን ማብራሪያው ጠቁሞ አድራጎቶቹ መቀጠላቸውንና እንደመጨረሻ እርምጃም የአንዳንድ የድርጅቱ ጥቂት ባለሥልጣናት ሃገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ለመጠየቅ መገደዱን አስታውቋል።

የመንግሥቱ ማብራሪያ ተፈፀሙ ያላቸውን ጥሰቶች “ውዥንብርን ለማፅዳት” በሚል ሲዘረዝርም “ሰብዓዊ እርዳታውን ለህወሓት አሳልፎ መስጠት፣ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን የፀጥታና ደኅንነት አሠራሮች መጣስ፣ የመገናኛ መሣሪያዎችን ህወሓት እንዲጠቀምባቸው ማስተላለፍ፣ “ህወሓት ለጦር ጉዳይና ተዋጊዎቹን ለማንቀሳቀስ ያዋላቸው” ያላቸው ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ወደ ትግራይ የገቡ ከ400 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲመለሱ የቀረቡ ጥያቄዎችን ችላ በማለት መቀጠል፣ እንዲሁም የተሳሳቱ መረጃዎችን ማሠራጨትና ሰብዓዊ ድጋፍን የፖለቲካ ጉዳይ ማድረግ” ሲል በአምስት ነጥቦች አስቀምጧል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ይህንን ጉዳይ እንዲመለከት አንዳንድ ሃገሮች መገፋፋታችው ኢትዮጵያን በጥልቅ ያሳዘነ መሆኑን ያመለከተው ይህ ማብራሪያ አድራጎቱ “በብሄራዊ ደኅንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብት በገሃድ የጣሰ ነው” ሲል ከስሶ ምክር ቤቱ ይህንን “ሰብዓዊ እርዳታን የፖለቲካ መጠቀሚያ የማድረግ አላስፈላጊ” ያለውን ጥሪ ውድቅ ያደርጋል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

መንግሥቱ በወሰደው እርምጃ ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ ይስተጓጎላል ብሎ መንግሥቱ እንደማያምን መግለጫው አመልክቶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እስካልተዳፈሩ ድረስ የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ ከወገነ ብዙ ተቋማት ጋር በመተባበር እንደሚቀጥል አስታውቋል።

እርዳታ የማድረሱ ሥራ እንዲቀጥል ለማድረግም የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞቹን የመቀየር ቅንቅስቃሴውን እንዲያፋጥን ይኸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ የወጣው ማብራሪያ ጠይቆ ተቀያሪዎቹ ፈጥነው ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መንግሥቱ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ፣ ከሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪውና ከሃገር ውስጥ ቢሮ ተጠሪው ጋር እንደሚሠራ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው የመንግሥቱቱ ድርጅትን ሰባት ባለሥልጣናት የማስወጣት ውሣኔ እንዳስደነገጣቸው ከትናንት በስተያ የተናገሩት የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ በጉዳዩ ላይ ከሃገሪቱ መሪዎች ጋር እየተነጋገሩ እንደነበረ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንም ከትናንት በስተያ ባወጡት መግለጫ የመንግሥቱን እርምጃ አውግዘው ውሣኔውን እንዲቀይር ያሳሰቡ ሲሆን ካለበለዚያ ግን ማዕቀብ እንዲጥሉ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለገንዘብና ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶቻቸው የሰጡትን ሥልጣን ተግባራዊ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG