ኢትዮጵያ እና ተገንጣይዋ ሶማሌላንድ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ባደረጉት የወደብ ስምምነት ዙሪያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት ንግግር መጀመራቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን አራት ባለስልጣናት ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ድርድሩ በሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማስተካከል የተደረገ ሙከራ መሆኑም ተገልጿል። ኢትዮጵያ በጥር ወር ከሶማሌላንድ 20 ኪሎሜትር ርዝማኔ ያለው ወደብ ለማግኘት እና በምላሹ ለሶማሌላንድ እውቅና ለመስጠት የገባችው ስምምነት ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻክር አድርጎታል።
ስምምነቱ ሕገወጥ መሆኑን የገለጸችው ሶማሊያ በምላሹ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገሯ ያባረረች ሲሆን፣ እስላማዊ አማፂያንን ለመዋጋት በሀገሯ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችንም ለማስወጣት እያስፈራራች ነው።
በጉዳዩ ላይ የሶማሊያን መንግስት ቃል አቀባይ፣ የቱርክን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የደህንነት አገልግሎት ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።
የሶማሌላን ቃል አቀባይ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል በሚደረገው ውይይት ላይ አለመጋበዛቸውን ተናግረዋል። እ.አ.አ በ1991 ነፃነቷን ካወጀች በኃላ በራስ ገዝ አስተዳደር ስር በንፅፅር የተሻለ ሰላም እና መረጋጋት ያላት ሶማሌላንድ እስካሁን ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት አልቻለችም።
የድርድሩ አላማ ግልፅ አለመሆኑን ለሮይተርስ የተናገሩት ሁለቱ ባለስልጣናት፣ መፍትሄ ለማግኘት ያለው ተስፋም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ ከስምምነቱ እስክትወጣ ድረስ ሶማሊያ እንደማትወያይ ይዛ ከነበረው አቋም ተለሳልሳለች የሚል ወሬ ቢኖርም፣ እውነቱ ግን ያንን አይመስልም" ያሉት አንደኛው ባለስልጣን፣ "ወደፊት የሚያራምድ ሁኔታ አይታየኝም፣ ከውይይቱ ብዙ አልጠብቅም" ብለዋል።
እ.አ.አ በ2011 ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሞቃዲሾን ከጎበኙ በኃላ፣ የጸጥታ ኃይሎች በማሰልጠን እና የልማት እርዳታዎችን በማቅረብ ቱርክ የሶማሊያ መንግስት የቅርብ አጋር ሆናለች።
ሁለቱ ሀገራት በየካቲት ወር የመከላከያ ውል የተፈራረሙ ሲሆን፣ በውሉ መሰረት አንካራ ሶማሊያ በውሃ ዙሪያ ያሉ ግዛቶቿን ማስከበር የሚያስችላትን የባህር ደህንነት ድጋፍ ታደርግላታለች። በተጨማሪም ቱርክ ሶማሊያ ውስጥ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና መሠረተልማቶችን የገነባች ሲሆን ሶማሊያውያን በቱርክ እንዲማሩ የሚያስችላቸው ነፃ የትምህርት እድልም ሰጥታለች።
በምትኩ ቱርክ በአፍሪካ እና ቁልፍ በሆነው የዓለም አቀፍ የባህር ላይ ማጓጓዝ መስመር አስተማማኝ ቦታ እንዲኖራት አስችሏታል።
መድረክ / ፎረም