በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ ኢትዮጵያ በራስገዟ አስተዳደር የባህር ኃይል ጦር ሰፈር እንዲኖራት አልፈቅድም አለች


ፎቶ ፋይል፦ ሞቃዲሹ፣ ሶማሊያ
ፎቶ ፋይል፦ ሞቃዲሹ፣ ሶማሊያ

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ በተገነጠለችው ሶማሌላንድ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ለመገንባት ያሰበችውን እቅድ ሶማሊያ መቼም እንደማትቀበለው እና፣ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረግ ከተቻለ ግን ለኢትዮጵያ የንግድ ወደብ አገልግሎት ለመስጠት እንደምታስብበት አንድ የሶማሊያ ከፍተኛ ባለሥልጣን አርብ እለት አስታወቁ።

የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ በጥር ወር እውቅና ለሌላት የሶማሌላንድ ራስገዝ አስተዳደር እውቅና ለመስጠት እና በምትኩ 20 ኪሎሜትር የሚሆን የባህር ዳርቻ በሊዝ ለመከራየት የተፈራረመችው ስምምነት ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ አስነስቷል።

ሶማሌላንድ እ.አ.አ ከ1991 ጀምሮ ራሷን ችላ የምትተዳደር ቢሆንም፣ ግዛቱን የራሷ አካል አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ ግን ስምምነቱ ህገወጥ ነው ስትል አልተቀበለችውም።

ይህንን አለመግባባት ለማርገብ ኬንያ ከጅቡቲ እና ከምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋራ በመመካከር፣ በቀጠናው ወደብ የሌላቸው መንግሥታት ወደቦችን በንግድ ውሎች ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ለመወሰን የባህር ላይ ስምምነት ሐሳብ ማቅረቧን አንድ የኬንያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሐሙስ እለት አስታውቀው ነበር።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር ለሮይተርስ በሰጡት ቃል ግን፣ በወደብ ተጠቃሚነት ዙሪያ የሁለትዮሽ ውይይት ከመደረጉ በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት ማፍረስ አለባት ብለዋል።

"ሶማሊያ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር እንዲመሰረት መቼም አትስማማም" ያሉት ኦማር፣ "በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ግን ሶማሊያ ለንግድ አገልግሎት ዝግጁ ናት" ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለው "ሉዓላዊነታችንን፣ የፖለቲካ ነፃነታችንን እና አንድነታችንን በመጠበቅ" የሀገሪቱን ፍላጎት እስካሟሉ ድረስ ሲማሊያ በሀሳቡ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኗንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው፣ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG