በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳኑ "መንፈንቅለ መንግሥት" ዓለም አቀፍ መግለጫዎች እየወጡ ነው


ሱዳን ዋና ከተማ ተቃዋሚዎች ጎዳና ላይ መንገድ በመዝጋት ጎማዎችን በማቃጠል ተቃውሟቸውን እየገለጡ
ሱዳን ዋና ከተማ ተቃዋሚዎች ጎዳና ላይ መንገድ በመዝጋት ጎማዎችን በማቃጠል ተቃውሟቸውን እየገለጡ

በሱዳን ከፍተኛው ባለሥልጣን ሌ/ጀኔራል አብድል ፈታ አልቡርሃን በሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ ያወጁ ሲሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱን ሲመራ የነበረው የሲቪልና ወታደራዊ የጋራ ምክር ቤት መበተኑን ተናግረዋል፡፡

አልቡርሃን መግለጫውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እና ሌሎች የልዕልና ምክር ቤት አባላት በወታደራዊ ኃይሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ከተገለጸ በኋላ ነው፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልኡክ ጀፍሪ ፊልትማን ዛሬ ባወጡት መግለጫ በሱዳን ወታደራዊ መንግሥት የሽግግር መንግሥቱን ሥልጣን እየወሰደ ነው በሚለው ዘገባ በእጅጉ ያሳሰባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፌልትማን በውጭ ጒዳይ ሚኒስቴር አፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ መደበኛ የትዊተር ገጽ ላይ ወታደራዊ የሥልጣን ነጠቃው የሱዳንን ህገመንግሥታዊ የሽግግር ድንጋጌ የሚቃረንና የዩናይትድ ስቴትስ ለሱዳን የምትሰጠውን እርዳታ ከጥያቄ ላይ የሚከት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በካርቱም ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ

“ወታደራዊ ኃይሉ በሱዳን የሲቪል መንግሥት ላይ የወሰደው እምርጃ ያሳሰበው መሆኑን” ገልጾ የሱዳንን የዴሞክራሲ ሽግግር አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት አውግዞታል፡፡

ኤምባሲው “የሱዳንን ሽግግር የሚያውኩ ሁሉም ተሳታፊዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እና የሲቪል መር መንግሥት እኤአ በ2019 የተካሄደውን አብዮት ግቦች ከግብ እንዲያደርስ እንዲያደርጉ” ጠይቋል፡፡

የአፍሪካ ህብረትም ባወጣው መግለጫ በቁጥጥር ስር የዋሉት የፖለቲካ መሪዎች እንዲለቀቁ አስታውቆ በወታደራዊና የሲቪል አስተዳደሮች መካከል ውይይት እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጎተሬዥ ባወጡት የትዊት መልዕክታቸው፣

"በሱዳን እየተካሄደ ያለውን የመንፈቅለ መንግሥት አወግዛለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክና ሌሎች ባለሥልጣናት በአስቸኳይ መለቀቅ አለባቸው" በብዙ ዋጋ ለመጣው የፖለቲካ ሽግግር ፣ የህግመንግሥቱ ቻርተር ሙሉ ክብር ሊሰጠው ይገባል፡፡የተባበሩት መንግሥታት ከሱዳን ህዝብ ጎን መቆሙን ይቀጥላል” ብለዋል፡፡ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክን መታሰር ተከትሎ ህዝባው ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡

ጋዜጠኛ ሚካኤል አቲት ከሱዳን ለቪኦኤ እንደተናገረው በሺዎች የሚቆጠሩ አዋቂዎችና ወጣቶች ወደ ከተማዪቱ ዋና ማዕከል እየሄዱ ነው፡፡ በየቦታው የተኩስ ድምጾች እየተሰሙና የተሽከርካሪ ጎማዎች ሲቃጠሉ መመልከቱንም ተናግሯል፡፡ በከተማው የግንኙነት መስመሮች የተቋረጡ ሲሆን፣ ብሄራዊ የአርበኝነት ዜማዎችን ከሚያሰሙ የመንግሥት ቴሌቭዥን ውጭ የተቀሩት የኢንተርኔትና የሬዲዮ ስርጭቶች መቋረጣቸውን አቲት ገልጿል፡፡

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በቤት ውስጥ እስር ሆነው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ሁኔታው የመንፈንቅለ መንግስት እንደሚመስል የሱዳን አገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ቤተሰቦችን በመጥቀስ ሮይተር እንደዘገበው የሱዳን ወታደሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን መኖሪያ ቤት የወረሩት ሰኞ ማለዳ ላይ ነው፡፡

አራት የካቢኔ ሚኒስትሮችና አንድ ሲቪል የገዥው የልዕልና ምክር ቤት አባል መታሰሩንም የአል ሃዳት ቴሌቭዥን መዘገቡ ተጠቅሷል፡፡

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን ሌሎች የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት መታሰራቸውን ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችም እንዲሁ መዘጋታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

XS
SM
MD
LG