በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን መፈንቅለ መንግሥት?


ፎቶ ፋይል፦ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ
ፎቶ ፋይል፦ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ

የመንግሥት ባለሥልጣናት ታሰሩ ኢንተርኔትና አውሮላን ማረፊያዎች ተዘግተዋል

የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በቤት ውስጥ እስር ሆነው በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ሁኔታው የመንፈንቅለ መንግሥት እንደሚመስል የሱዳን አገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

ቤተሰቦችን በመጥቀስ ሮይተር እንደዘገበው የሱዳን ወታደሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን መኖሪያ ቤት የወረሩት ሰኞ ማለዳ ላይ ነው፡፡

አራት የካቢኔ ሚኒስትሮችና አንድ ሲቪል የገዥው የልዕልና ምክር ቤት አባል መታሰሩንም የአል ሃዳት ቴሌቭዥን መዘገቡ ተጠቅሷል፡፡

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን ሌሎች የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣናት መታሰራቸውን ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችም እንዲሁ መዘጋታቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣኑን መረከቡን የሚደግፉ ወገኖች ይህ አብዮቱ ትክክለኛ መንገድ የሚያስተካክል ነው ብለው ቢያስቡም ሌሎች ሥልጣንን ወደ ሙሉ ሲቪል አስተዳደር እንዲተላለፍ ለሚፈግሉት ግን ይህ በርግጠኝነት እንደ መሰናክል ተደርጎ ይወሰዳል” ሲል፣ ሰይድ ኢስማኤል ኩሽኩሽ የተባለ ገለልተኛ ጋዜጠኛና ፣ የቀድሞ የኒዮርክ ታይምስ የምስራቅ አፍሪካ ዘጋቢ፣ ለቪኦኤ ተናገሯል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ያገለገሉት ሀምዶክ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና ዲፕሎማት ሲሆኑ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተየሰየሙት እኤአ ነሀሴ 2019 ላይ ነበር፡፡ ሀምዶክ ሥልጣኑን የተረከቡት የረጀም ጊዜ አምባገነን መሪ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በአገሪቱ በተቀሰቀሰው መጠነ ሰፊ ተቃውሞ ከሥልጣን ተወግደው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ነበር፡፡ ሱዳን በሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ለሚደረገው ምርጫ እየተዘጋጀች የነበረ ሲሆን በህገመንግሥቱ መሠረት ሀምዶክ መወዳደር አይችሉም ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ሀምዶክ ከአገሪቱ ወታደራዊ ክፍል ብርቱ ተቃውሞ ገሟቸዋል፡፡ እኤአ መስከረም 21 የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ደጋፊዎች የነበሩ ወታደሮች ቁልፍ ቦታዎችንና ድልድዮችን በመዝጋት ሥልጣን ለመያዝ ሞክረው ነበር፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራው የከሸፈ ሲሆን በርካታ ወታደሮችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርገዋል፡፡

ባላፈው ሰማንት በርካታ ተቃዋሚዎች ወደ አደባባይ በመውጣት የወታደራዊውን መንግሥት ወደ ሥልጣን መመለስ ተቃውመዋል፡፡ “ይህ አገር የኛ ነው መንግስታችንም የሲቩሉ ነው” የሚሉ መፈክሮችንም ሲያሰሙ ተደምጠዋል፡፡

ህዝባዊ ተቃውሞን በማስተባበር ከሚታወቀው የሠራተኛ ማህበራት ያሉበት ሱዳን ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ ሰኞ ባደረጉት ጥሪ ህዝቡ ወደ አደባባይ ወጥቶ አውራመንገዶችን በመዝጋት የሽግግሩን መንግሥት እንዲታደግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሱዳን ጉዳይ እውቀት ያላቸውና የቀድሞ የዋይት ሀውስ የአፍሪካ ድሬክተር የነበሩትና አሁን በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕክል ከፍተኛ አጥኚ የሆኑት ካሜሮን ሃድሠን “ ይህ በሱዳን ለተሞከረው የዴሞክራሲ ሂደት ትልቅ ኪሳራ ነው” ብለዋል፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የሚመስለው ድርጊት የመጣው በአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፊልትማና ከሱዳን መሪዎች ጋር ለሁለት ቀናት ተገናኝተው ዩናይትድ ስቴትስ ለዴሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር የምትሰጠውን ድጋፍ ካሰመሩበት በኋላ ነው፡፡

ሀድሰን፣ የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች የሽግግር መንግሥቱን ዓላማ ስለማሳካቱ ለፊልትማን ቃል ገብተውላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ሀድሰን ለቪኦኤ ሲናገሩ “ዩናይትድ ስቴትስ ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ በአብዛኛው በሱዳን በዲሎማሲው ረገድ አገሪቱ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ እንድተሸጋገር ኢንቨስት አድርጋለች” ብለዋል፡፡ አይይዘውም “በቻድ ማሊ ጊኒና ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ የነበረባቸው ነበሩ ይሁን እንጂ አንዳቸውም ዩናይትድ ስቴትስ ለሱዳን የሰጠቸውን የዲፕሎማሲ ጥረት ያህል እንኳ ለማገኘት የተቃረቡ አልነበሩም፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡

ጋዜጠኛው ኩሽኩሽም “አልበሽር ከተወገዱበት ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ አብዛኞቹ ሱዳኖች የነበራቸው ትልቁ ስጋት የሱዳን አብዮት እጣ በአካባቢው ከነበሩ ሌሎች አገሮች አብዮት ጋር ተመሳሳይ እንዳይሆን ምናልባትም በአሁኑ ሰዓት ከሌሎችም የከፋ እንዳይሆን ነው” በማለት ያለውን ስጋት ገልጧል፡፡

XS
SM
MD
LG