ሶማሊያና ቱርክ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ የማውጣት ስምምነት መፈራረማቸውን የሁለቱም ሀገራት ባለሥልጣናት ዛሬ አስታውቀዋል።
ቱርክ ውስጥ ትላንት የተፈረመው ስምምነት፤ ሁለቱ አገራት በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ንግድ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር የሚያጠናክር እንደሆነ የሶማሊያ የፔትሮሊየም እና የማዕድን ሚንስትር አብድራዛቅ ሞሃመድ አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ በ X ማኅበራዊ መድረክ ላይ እንዳስታወቁት፣ ቱርክ በባሕር እና በመሬት ላይ የነዳጅ ዘይት እና ጋዝ ፍለጋ እንዲሁም የማውጣት ሥራ እንደምታከናውን ገልፀዋል።
የምርት መከፋፈልን በተመለከተ ዝርዝር ስምምነት ባይፈጽሙም፣ ትናንት የተፈረመው የ10 ዓመት ስምምነት ግን አጠቃላይ ስምምነት እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
የቱርክ ፕሬዚደንት ራሲፕ ታይብ ኤርዶዋ ከ13 ዓመታት በፊት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2011ዓ.ም ሶማሊያ በረሃብ በተመታችበት ወቅት ጉብኝት ካደረጉ ወዲህ፣ ቱርክ የሶማሊያ ዋና አጋር ሆናለች፡፡
ቱርክ የሰብዓዊ ድጋፍ እና የበጀት ድጎማም ስትሰጥ ቆይታለች፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት ደግሞ ወታደራዊ ማሠልጠኛ በመገንባት፣ የሶማሊያ ፀጥታ ኃይሎችን ስታሠለጥን ከርማለች፡፡
መድረክ / ፎረም