በታሪክ በድብቅ ከወጡ ሁሉ በግዙፍነቱ ወደር እንደሌለው የተጠቀሰው እና ሞሳክ ፎሴካ ከሚባል የፓናማ ኩባኒያ የወጣው ግዙፍ ሰነድ ከዓለም ዙሪያ አስራ ሁለት የሀገር መሪዎች ጨምሮ አንድ መቶ አርባ ሶስት የፖሌቲካ ባለስልጣናትን የሚነካ የፊናንስ ታሪክ ዘክዝክኳል። ከአፍሪካ የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ሰብሳቢ ዳኛ፣ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ጄኮፕ ዙማ የወንድም ልጅ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ መንቲያ እህት ስም የሚመለከት ሰነድ አለበት። በነዳጅ የከበረችው የናይጄሪያ ናይጄር ዴልታ የቀድሞ አገረ ገዢ፣ የሌላዋ የነዳጅ ባለጸጋ ሃገር የአንጎላ የነዳጅ ሚኒስትር፣ የሟቹ የጊኒ መሪ ላንሳና ኮንቴ ባለቤት እንዲሁም የቀድሞ የተ. መ. ድ. ዋና ጸሓፊ ኮፊ አናን ልጅ ስምም በፓናማው ሰነድ በተጋለጡት የባንክ ሂሳቦች ስማቸው ተነስቷል።
ባሁኑ ጊዜ እንግሊዝ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙት በነዳጅ የከበረችው የናይጄሪያ ናይጀር ዴልታ ክፍለ ሀገር የቀድሞ ኣገረ ገዢው እና የመወሰኛው ምክር ቤት ፕሬዚደንት ቤተሰብ ስም በፓናማው ሰነድ ከተጠቀሱት ታዋቂ ሰዎች የገለጹት ስታንሊ አቾኑ ሰነዶቹ ቀድሞውኑም የምናውቀውን ጉዳይ ነው ያረጋገጡልን ብለዋል።
"በአፍሪካ በጠቅላላ ያለ ነገር ነው፣ ደቡብ አፍሪካ ሩዋንዳ ሌሎችም ተነካክተዋል። ይህ ሰነድ ያረጋገጠልን የአፍሪካ መሪዎች የህዙቡን ገንዘብ እንደራሳቸው የባንክ ሂሳብ ቆጥረው እንደሚዘርፉት ነው። የአፍሪካ ህዝብ ገንዘቡ የማያስፈገው ይመስል።" ብለዋል
የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ሙስና ላይ ሊዘምቱና የተመዘበረው የህዝብ ገንዘብ ለማስመለስ ቃል ገብተው ነበርና ይህ ሰነድ ለዘመቻቸው በማስረጃነት አንደሚጠቅማቸው ስታንሊ ኦቹኑ ገልጸዋል።
"ኣዎ ይሄ ኣገሪቱ ባለፉት ዓመታት ምን ያህል የአስተዳደር ብልሹነት ሰፍኖ እንደነበር ያመለክታል። የመንግስት ገንዘብ በህዝብ በተመረጡም በመንግስት በተሾሙም ባለስልጣናት ሲዘረፍ ኣንደነበር ፕሬዚደንቱ በቅርቡ የተናገሩትን የሚያረግግጥ ነው።" ብለዋል።
በተጨማሪም፣ "ስለዚህ ሰነዱ ለጸረ ሙስና ዘመቻው በማስረጃነት ይጠቅማል። ገንዘቡንም ለማስመለስ ለምንወስደው ርምጃ የምናመራበትን አቅጣጫም ይጠቁመናል።" ብለዋል።
በሀገራቸው በሙስና ወንጀል ክስ ተወጥረው የሚገኙት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚደንት ጄካፕ ዙማም በወንድማቸው ልጅ ስም ከሀገር ውጭ ባለ ባንክ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ መኖሩን የፓንማው ሞሳክ ፎንቴጋ ሰነድ ያጋልጣል ። በሙስና ቅሌት በተደጋጋሚ የሚወነጀሉት ዙማ በቅርቡም ለቤታቸው ምሳደሳ ያዋሉትን የመንግስት ገንዘብ እንዲመልሱ በፍርድ ቤት የተወሰነባቸው መሆኑን ያስታወሱት ስታንሊ ኦቹኑ፣ አሁን ደግሞ በበፓናማው ሰነድ ስማቸው መነሳቱ ደቡብ ኣፍሪካውያን ኣንድ ርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ነው ብለዋል።
"በኔ አስተያየት ጉዳዩ ደቡብ ኣፍሪካን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ደቡብ አፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአህጉሪቱ ትልቅ ሚና የምትጫወት ሀገር በመሆንዋ አፍሪካውያን በአርእያነት የሚመለከቷት ስለሆነ በሙስና ቅሌት የተበተበ መሪ ሊኖራት አይገባም።"ብሏል።
ውጭ ሃገር ወዳሉ ተቁዋማት የሚሸሸው አብዛኛው ገንዘብ የሚሸሰው ግብር እንዳይከፈልበት ቢሆንም አፍሪካን ያየን እንደሆን አሉ ።
"በተለይ በአፍሪካ ግብር ላለመክፈል ተብሎ የተፈጸመ ብቻ ኣድርጌ አላየውም። የመንግስት ገንዘብ የዘረፉ ሰዎች በውጭ ሃገር ባለ ኣካል የሚንቀሳቅሱት ገንዘቡን በመንግስት ስራቸው በሚያገኙት መደበኛ ደመዎዝ ያጠራቀምኩት ነው ሊሉ ስለማይችሉ ነው።" ብለዋል።
አስራ አራት ሽህ በላይ ደምበኞች ያሏቸውን ከሁለት መቶ ሽህ የሚበልጡ ኩባኒያዎች የሚመለከተውና ዕሁድ ዕለት ይፋ የሆነውና ማንነቱ ባልታወቅ ወገን በድብቅ የወጣው የደለበ ሰነድ ተከትሎ ከወዲሁ ክትትል የጀመሩ መንግስታት እንዳሉ ተመልክቷል።
በሌላ በኩል የቻይና መንግስት በፓናማው ሰነድ ዙሪያ የሚወጡ ዘገባዎች ላይ ቁጥጥር እያደረገ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ብሎታል። ክሬዲት ሲዊስና ኤችኤስቢሲ (hsbc) የተባሉት ሁለት ትላልቅ ዓለም አቀፍ ባንኮች ደምበኞቻችን ታክስ እንዳይከፍሉ ለመርዳት በውጭ ሃገር የባንክ ሂሳብ የመጠቀም ወንጀል አልፈጸምንም ሲሉ አስተባብለዋል። ፈረንሳይ ፡ አውስትሬሊያ፣ ስዊድንና ኔዘርላንድስ የየራሳቸውን ምርመራ መጀመራቸውን ይፋ አድርገዋል።
የቪኦኤው ጄምስ በቲ የናይጄሪያ ፌደራላዊ መንግስት በጀት ለህዝቡ ጠቀሜታ መዋሉን ለማረጋገጥ የሚሰራ ድርጅት መስራች የሆኑትን ስታንሊ ኦቾሉ አነጋግሮ ያጠናቀረውን ዘገባ ቆንጂት ታዬ አቅርባዋለች።