በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩናይትድ ስቴትስ ለፕረዚዳንትነት በሚደረገው የምርጫ ውድድር ትላንት ትኩረት ስበው የዋሉት ሚሽገንና ሚሲሲፒ ናቸው


በሚሽገን በተካሄደው ቀዳሚ ምርጫ ዲሞክራቱ በርኒ ሳንደርስ በአጠቃላይ ድምጽ እየቀደሙ ያሉትን ሂለሪ ክሊንተን ለጥቂት አሸንፈዋል። በሚሲሲፒ ደግሞ ሂለሪ ክሊንተን ሳንደርስን በብዙ ድምጽ ልቀዋል። ከሪፑብሊካውያን ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱም ክፍለ-ግዛቶች በማሸነፍ ቀጥለዋል።

በርኒ ሳንደርስ በሚሽጋን ማሸነፋቸው የዲሞክራስያዊ ፓርቲን ውክልና አግኝቶ ለሀገሪቱ ፕረዚዳንትነት ለመወዳደር በዲሞክራቶች መካከል የሚካሄደው ውድድር እንደሚቀጥል አመላክቷል። እስካሁን ባለው ጊዜ ቀዳሚ ቦታ የያዙት ክሊንተን መሆናቸው ይታወቃል።

“የዛሬው ሁኔታ የሚያሳየው የበርኒ ሳንደርስ የምርጫ ዘመቻ፣ እየተነጋገርንበት ያለነው ህዝባዊ አብዮት፣ እያወራንበት ያለለነው ፖለቲካዊ አብዮት በያንዳንዱ የሀገሪቱ ክፍል ጠንካራ መሆኑን ነው።” ብለዋል ሳንደርስ።

ሂለሪ ክሊንተን በሚሲሲፒ በብዙ ድምጽ አሸንፈዋል። በሚሽጋንም የተወካዮችን ድጋፍ ከሳንደርስ ይጋራሉ። በመጪው ሳምንት በአምስት ትልልቅ ክፍለ-ግዛቶች በሚካሄደው ቀዳሚ ምርጫም በተወካዮች ውክልና ረገድ በሰፌው እየመሩ ነው። "ለኔ ከሰራችሁ እኔን ከመረጣችሁ ለናንተ እለፋለሁ። በእያንዳንዷ እለት ጠንክሬ እሰራለሁ።” ይላሉ ክሊንተን።

በሪፓብሊካውያን በኩል ዶናልድ ትራምፕ በሚሲሲፒና በሚችጋን በማሸነፋቸው የሪፑብሊካዊው ፓርቲ ውክልና ወደ ማግኘት የሚያመራቸው አንድ እርምጃ ሄደዋል።

ትራምፕ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ በሳቸው ላይ አሉታዊ የሆኑ ማስታወቅያዎች በቴሌቪዥን ሲታዩ የቆዩ ቢሆንም በማሸነፋቸው ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

“ክፉኛ አጥቅተውኛል። እያንዳንዳቸው ያጠቁኝ ስዎችም ሄደዋል። ለዚህም ኩራት ይሰማኛል። በሀገራችን መኖር ያለበት ይህ ነውና።”ብለዋል ትራምፕ።

የኦሃዮ ክፍለ-ግዛት አስተዳዳሪ ጆን ኬሲችና ሴኔተር ቴድ ክሩዝ ወደ ኋላ ቀርተዋል። ኬሲች ደጋፊዎቻቸው በመጪው ሳምንት በክፍለ-ግዛታቸው ወደ ሚካሄደው ቀዳሚ ምርጫ አሻግረው እንዲያዩ አሳሳበዋል።

“ሰዎች በአዎንታዊ መንፈስ የሚካሄድ የምርጫ ዘመቻን መሸለም የጀመሩ ይመስለኛል። በፖለቲካው አለም ማድረግ ያለባችሁ ይህን ነው በማለት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት። ለአንድ ሳምንት ጠብቁና በኦሃዮ ክፍለ-ግዛት እናሸንፋለን እናም ሁኔታዎች ይለወጣሉ።”ሲሉ ገልጸዋል ኬሲች።

በአይዳሆው ቀዳሚ ምርጫ ያሸነፉት ቴድ ክሩዝ ትራምፕ በብሄራዊ ደረጃ ያላቸው ድጋፍ እየወረደ መሆኑን የድምጽ መለክያ አሀዞች መግለጻቸውን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

“ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ትንንቅ ላይ መሆናችንን የሚያሳዩ አሃዞች ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ዎል ስትሪት ጆርናል ላይ እንደወጡ እናውቃለን።”ብለዋል ቴድ ክሩዝ።

በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ላይ ቀዳሚ ምርጫ ከሚካሄድባቸው አምስት ክፍለ-ግዛቶች ዋናዎቹ ፍሎሪዳና ኦሃዮ ናቸው።

የሪፓብሊካውያን ፕረዚደንታዊ እጩ ማርኮ ሩብዮ
የሪፓብሊካውያን ፕረዚደንታዊ እጩ ማርኮ ሩብዮ

የአሜሪካ ድምፅ ብሄራዊ ዘጋቢ ጆም ማሎን የትላንቱን ቅድመ-ምርጫ አጠቃላይ ውጤት አጠናቅሯል። አዳነች ፍሰሀየ ታቀርበዋለች።

ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG