በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፑቲን ለአፍሪካ ሀገራት እህል ለመላክ ቃል ገቡ


ፑቲን ለአፍሪካ ሀገራት እህል ለመላክ ቃል ገቡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:47 0:00

ፑቲን ለአፍሪካ ሀገራት እህል ለመላክ ቃል ገቡ

የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን ለአፍሪካ ሀገራት እህል እንደሚልኩ ሴንት ፒተርስበርግ ላይ ለተሰበሰቡት የአፍሪካ መሪዎች እና ባለሥልጣናት ቃል ገቡ፡፡ ሀገራቸው ከዩክሬን የእህል አቅርቦት በጥቁር ባህር በኩል እንዲወጣ ካስቻለው የጥቁር ባህር ስምምነት በመውጣቷ የተደቀነውን ችግር ለመቀልበስ “በሽያጭ ወይም ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሀገሮች ደግሞ በነጻ እህል እንልካለን” ብለዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የሩስያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሀገራችን ከዩክሬን የሚላከውን እህል ተክታ እንደምትልክ ካሁን ቀደም ተናግሬለሁ፡፡ በሽያጭም በጣም ችግረኛ ለኾኑት ሀገሮች ደግሞ በርዳታ መልክ እንልካለን፡፡ ይህ ደግሞ ዘንድሮም እጅግ የተትረፈረፈ ምርት ይኖረናል ብለን ስለምንጠብቅም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡ ዓለም አእቀፍ የምግብ ቀውስ እንዳይከሰት ከፍተኛ ጥረት በማደረግ ላይ ነን ሲሉ ፑቲን አክለው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በዋሽንግተን ኋይት ሐውስ የሩስያው መሪ እጅግ ድሃ የሆኑትን ሀገሮች እየጎዳ ያለውን የምግብ ቀውስ እፈታለሁ ማለታቸውን አጣጥሎታል፡፡

“የምግብ ዋጋ እንዲህ የሚዋዥቀው፣ ሀገሮቻችሁ የባሰ የረሃብ ችግር ውስጥ የሚወድቁት በኔ ምክንያት ነው”

የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ፑቲን ለአፍሪካ መሪዎቹ “የምግብ ዋጋ እንዲህ የሚዋዥቀው፣ ሀገሮቻችሁ የባሰ የረሃብ ችግር ውስጥ የሚወድቁት በኔ ምክንያት ነው” ብለው ይነግሯቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉም የብሄራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባዩ አክለዋል፡፡

ጃን ከርቢ አክለውም “ እያየነው ላለነው የምግብ ዋጋ መዋዠቅ ተጠያቂው ከዩክሬን የእህል አቅርቦት ማስወጣት ይበልጡን አስቸጋሪ እየሆነ የሚሄደውም በሚስተር ፑቲን ምክንያት ነው፡፡ እውነቱን ይነግሯቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ መንገርም አለባቸው” ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ሩስያ ለአንድ ዓመት ገደማ የዘለቀውን የጥቁር ባህር የዕህል ማጓጓዝ መርሐ ግብር ስምምነት አላድስም ማለቷ ይታወሳል፡፡ እኛ የምንልከው እህል እና ማዳበሪያ በስምምነቱ በትክክል አልተያዘልኝም ነው ያለችው፡፡ በጥቁር ባሕር ላይ የሚያልፉ መርከቦች ወደዩክሬን የጦር መሣሪያ የሚያጓጉዙ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጥቃት ልናደርስባቸው እንችላለን ስትልም አስታውቃለች፡፡

ፑቲን የምግብ አቅርቦት የመላክ እቅዳቸውን ሀገራቸው ከአፍሪካ ሀገሮች እና ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮኑ የአህጉሪቱ ሕዝብ ጋራ ግንኙነቷን ለማጠናከር እየተጠቀሙበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የኋይት ሐውስ የብሔራዊ ጸጥታ ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ የጥቁር ባሕር ስምምነቱ እንዳይራዘም ያደረጉት ውሳኔ አፍሪካ ሀገሮች የሚያስከተለውን ጉዳት ለመሸፋፈን በጥድፊያ የሚያደርጉት ሙከራ ይመስላል፡፡ ተገቢ ነው ወይ? እንቀበለዋለን ወይ? የሚለውን እያንዳንዱ ሉዓላዊ ሀገር ለራሱ የሚወስንበት ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡

ሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ውስጥ የተከፈተው የሩስያ አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ሁለተኛው ጉባኤ ሲሆን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 ዓም በተካሄደው በመጀመሪያው ጉባኤ ላይ 43 መራሄ መንግሥታት የተገኙ ሲሆን በዚህኛው የተገኙት 17 ብቻ ናቸው፡፡ ክሬምሊን ቤተ መንግሥት የመሪዎቹ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰው በምዕራባውያን ተጽዕኖ የተነሳ ነው ብሏል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG