በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ የሩሲያ - አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን ለማስተጓጎል ሞክራለች ስትል ሞስኮ ከሠሠች


ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን

ሁለተኛውን የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን ለማስተናገድ የተዘጋጀችው ሞስኮ፣ “ምዕራባውያን በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ፣ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ፣ ጉባኤውን ለማስተጓጎል ሞክረዋል፤” ስትል ከሠሠች።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ እንደተናገሩት፣ “የአፍሪካ ሀገራት በጉባኤው እንዳይሳተፉ ለማድረግ ሲባል፣ ‘ከአሁን ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ጫና’ ተደርጎባቸዋል፤” ብለዋል።

በመሠረቱ የአፍሪካ መንግሥታት፣ በተለያዩ መስኮች ለሚያደርጓቸው የትብብር እና የጋራ ግንኙነቶች፣ አጋሮቻቸውን መምረጥ እና መወሰን እንደሚችሉ የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ ይህን “ሉዓላዊ መብታቸውን ግን አይቀበሉም፤” ብለዋል።

ከነገ ሐምሌ 20 እስከ 21 ቀን፣ በሴንት ፒተርስበርግ የሚካሔደው የዚኹ ጉባኤ አዘጋጅ የሩሲያው መሪ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ከየሀገራቱ መሪዎች ጋራ፣ ከንግድ እና የደኅንነት ጉዳዮች እስከ እህል አቅርቦት ድረስ ባሉት ዐበይት ጭብጦች ላይ ትኩረት ያደረጉ የተናጠል ውይይቶች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ምዕራባውያኑም ሳይቀሩ እንዳስተጋቡት፣ ይህ አህጉር አቀፍ የመሪዎች ጉባኤ፣ ሩሲያ በዩክሬን ከሚካሔደው ጦርነት ጀርባ፣ ተጽእኖ ማድረግ የሚያስችላትን ዐቅም ለማጎልበት የምታደርገው የተቀናጀ ጥረት አካል ነው፤ ተብሏል።

የዘንድሮው የአፍሪካ - ሩሲያ የመሪዎች ጉባኤ የሚካሔደው፣ ሞስኮ፣ ባለፈው ሳምንት፣ “የጥቁር ባሕር የእህል ምርት ስምምነት” በመባል ከሚታወቀውና ዩክሬይን፣ የእህል ምርቷን ከወደቦቿ ወደ ዓለም ገበያ ለመጫን ከሚፈቅድላት አሠራር መውጣቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ነው።

ስምምነቱ፣ ዩክሬን፥ የእህል ምርቷን፣ ከጥቁር ባሕር ወደቦቿ ወደተለያዩ የአፍሪቃ አገሮች ለመላክ አስችሏት ነበር።

ይህን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡት ፔስኮቭ፣ “ከአፍሪካውያን ጋራ በመሰባሰብ፣ በተለይም ስለ ምግብ አቅርቦት ግዴታዎቻችንና የእህል ምርት ለማስተላለፍ የተደረሰው ስምምነት ውድቅ ስለኾነባቸው ምክንያቶች፣ ሩሲያ፥ የዓለም ገበያዎችን ለመደገፍ ስለምታደርገው ጥረት እና ስለምትከተለው ሓላፊነት የተመላበት አቀራረብ፣ እንዲሁም የትኞቹ ግዴታዎች በማን ሳይሟሉ ቀሩ በሚሉት ጉዳዮች ላይ መወያየት መቻል፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ነው፤” ብለዋል።

ሩሲያ በተጨማሪም፣ በዩክሬን ለዓለም ገበያ ይቀርብ የነበረውን ምርት ለመተካትና አሁን ባለው ኹኔታ የተፈጠረውን የምግብ እጥረት ለማካካስ፣ ለድኻ የአፍሪቃ አገሮች፣ የእህል ምርቷን በርካሽ አልያም በነፃ ማቅረብ ስለመቻሉም ጠቁማለች።

በተያያዘም፣ “49 የአፍሪካ ልዑካን፣ በሴንት ፒተርስበርጉ የመሪዎች ጉባኤ እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል፤” ሲሉ፣ አንድ የሩሲያ ዲፕሎማት፣ በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ መናገራቸውን፣ የሩስያው ታስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ከእነኚኽም ውስጥ ገሚሱ ሀገራት፣ በመሪዎቻቸው ይወከላሉ፤ ተብሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG